በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጽያውያን ከካምፕ እንዲወጡ በመደረጋቸው ለብርድና ለሀሩር መዳረጋቸውን ገለጡ

ህዳር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢሳት  ሬዲዮ  ያናገራቸው  በሊቢያና  በቱኒዚያ  ድንበር  ላይ  የሚገኙ  ኢትዮጽያውያኖች  እንደገለፁልን  የተባበሩት  መንግስታት  የስደተኞች  ከፍተኛ ኮምሽን  ጉዳያቸውን  የያዘ  ቢሆንም  ከፊሎቹን  በስደተኝነት  ተቀብሎ  ከፊሎቹን  ሳይቀበላቸው  በመቅረቱ  ለከፍተኛ  ችግር  ተዳርገዋል ።

በሊበለያ  ከ10  እስከ  20  አመት  የኖሩ  ነገር ግን  በሊቢያ  በተነሳው  ህዝባዊ አመጽ  ወደካምፕ  እንዲገቡ  ከተገደዱት  ከነዚህ  ኢትዮጽያዊያን  መካከል  የሁለት  ልጆች  እናት  የሆነችው  ኢትዮጽያዊ  እንደገለፀችልን  ያለ መጠለያና ያለ ምግብ  በቱኒዝያ  ድንበር  ለከፍተኛ  ችግር  ተዳርጋለች ።

 

ለኢትዮጽያውያንና  ለአለም  አቀፍ  ማህበረሰብ  የድረሱልን  ጥሪ  ያቀረቡት  ኢትዮጽያውያኑ  ከተባበሩት  መንግስታት  የስደተኞች  ኮምሽንና  ከቱኒዚያ  መንግስት  የተሰጣቸው  ምላሽ  የለም  ወይንም  በጣም  አዝጋሚ  ነው ።

ቀድሞ  በካምፑ  ውስጥ  በርካታ  ኢትዮጽያውያን  እንደነበሩ  የገለፁት  ስደተኞቹ  90 ከመቶ  የሚሆኑትን  የተባበሩት  መንግስታት  የስደተኞች ኮሚሽን  የተቀበላቸው  ሲሆን  አልቀበልም  ወደ  ሀገራችሁ  ተመለሱ  ያላቸው  ግን  ወደ  ሀገር  መመለስ  የማይችሉ በመሆኑ  ከካንምፑ  ወተው  በሜዳ  ተበትነው  የሚገኙ  መሆናቸውን  አመልክተዋል።