የመከላከያ ሰራዊት አዲሱን መንግስት እንዲቀበሉ ለማሳመን የሚደረገው ግምገማ ቀጥሎአል

ጥቅምት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት የመከላከያ ሰራዊት ምንጮች እንደገለጡት  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  ካረፉ እና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከተሾሙ በሁዋላ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚካሄደው ግምገማ ተጠናክሮ ቀጥሎአል።

ከፍተኛ የጦር አዛዦች ግምገማ መጠናቀቁን የጠቆሙት ምንጮች፣ ግምገማው ወደ መካከለኛና ተራ ወታደሮች እየወረደ ነው።

በምስራቅ እዝ የሚገኙ እስከ ኮሎኔልነት ማእረግ ያላቸው መኮንኖች ሀረር ውስጥ ልዩ ስፍራው ቤተመንግስት በሚባለው ቦታ ከፍተኛ ግምገማ እያደረጉ ነው። የግምገማው ዋና አጀንዳ አቶ ሀይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው  በፊት ለ34 ወታደራዊ መኮንኖች ስለተሰጠው ማእረግ፣ ስለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር እና ስለመለስ ራእይ መሆኑ ታውቋል።

ሀረር ውስጥ በሚካሄደው ግምገማ የአመለካከት ልዩነቶች መታየታቸውንና ግልጽ ሆኖ ባይወጣም ክፍፍል መፈጠሩን ምንጮች ገልጠዋል።

በቅርቡ ለ34 ወታደራዊ መኮንኖች ከፍተኛ የማእረግ እድገት ሲሰጥ፣ 29ኙን የማእረግ እድገት የወሰዱት የህወሀት ጄኔራሎች መሆናቸው በሌሎች ብሄሮች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ቅሬታ መፍጠሩ ታውቋል።አሁን የሚካሄደው ግምገማ በዋነኝነት ይህን ቅሬታ ለመፍታት መሆኑ ታውቋል።

ግምገማው  ሹመቱን የማይቀበሉትንና በአዲሱ አስተዳዳር ላይ ቅሬታ ያላቸውን መኮንኖች በመለየት ለመውሰድ ተብሎ የተዘጋጀ ነው በሚል ፍርሀት የሌሎች ብሄር ተወላጅ መኮንኖች አስተያየቶችን ከመስጠት መቆጠባቸውንና አስተያየትም ከሰጡ የድጋፍ አስተያየት ብቻ በመስጠት ተቃውሞአቸውን በውስጣቸው መያዛቸውን ምንጫችን ገልጠዋል።

ከፍተኛ አዛዦች በተሳተፉት ግምገማ የአየር ሀይል ዋና አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ሞላ ሀይለማርያም  ከስልጣን መባረራቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትግራይ ታይቶ በማይታወቅ ስብሰባ ተጠምዳ መክረሙዋን ሰንደቅ ዘግቧል።

 

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) ከተመሰረተ በኋላ ከተደረጉ ሕዝባዊ ሰብሰባዎች ሁሉ ግዙፍ ነው የተባለለት ስብሰባ በመላ ትግራይ ሲካሄድ መሰንበቱን ጋዜጣው ዘግቧል

 

የስብሰባው ዋና ትኩረት ፦<<የመለስን ራዕይ  ማስቀጠል>> የሚል ሲሆን፤ በቅድሚያ በከፍተኛ አመራሮች ሲካሄድ የሰነበተው ስብሰባው በየደረጃው ላሉ መዋቅሮች እንዲወርድ ተደርጓል።

 

ጋዜጣው  ምንጮቹን በመጥቀስ እንዳለው  በትግራይ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ሳይካፈል አልቀረም።

 

በዚሁ ስብሰባ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሚሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች  በሙሉ ተካፍለዋል።

 

ስብሰባው በሴቶችና በወንዶች እንዲሁም በባለሀብቶች ተለይቶ መካሄዱን የዘገበው ጋዜጣ፤ በስብሰባው ለተካፈሉ በቀን እስከ 35 ብር አበል እንደተከፈለም  ጠቁመዋል።

 

በዚህም መሰረት ለ አንድ  ቀን ስብሰባ  ብቻ   35 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲደረግ ሰንብቷል።

 

በ እያንዳንዱ ቀን 35 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ስብሰባ ለስንት ቀናት እንደቆየ ጋዜጣው አላመለከተም።

 

በዚሁ ስብሰባ በክልሉ ቀደም ሲል ከነበረው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በተጨማሪ አዳዲስ የህዝብ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተመልክቷል።

 

በዚህም መሰረት አንድ ለአምስት አደረጃጀት (አንድ ህዋስን) በስድስት ህዋስ በማጣመር- ስድስቱን ህዋሳት በአንድ ላይ የሚጠረንፉ አራት አራት  ሰዎች እንዲዋቀሩ ተደርጓል። በዚህም መሰረት 4ለ30 የተባለ አዲስ አደረጃጀት መፈጠሩም ተገልጿል።

ዜና 2