አንድ የሲቪል ሰርቪስ ባለስልጣን ሃገር ከዱ

ጥቅምት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስን ሕመምና ሕልፈት ተከትሎ ስርአቱን እየከዱ የሚሸሹ ባለስልጣናት በተለይም የሕውሐት አባላት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ከኢትዮጲያ ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች እያመላከቱ መጥተዋል።

በዚህ መሰረት የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ሕውሐት አባል አቶ አታክልቲ ሐጎስ ከነቤተሰባቸው ከሃገር መሰደዳቸው ታውቋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት አቶ አታክልቲ ሐጎስ ከነቤተሰባቸው ካናዳ መግባታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ለካናዳ መንግስት የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
እኚህ የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ባልስልጣን ከነቤተሰባቸው ካናዳ ከገቡ ከወር በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን ከስራ ገበታቸው ከተለዩ 2 ወር እንዳለፈው አመልክተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ ሕዝብ ግኑኝነት ስልክ የደወልን ቢሆንም የቢሮው ስልክ ሊነሳ አልቻለም።
በሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊው የእጅ ስልክ ደውለን የሚከተለውን የተቀረጸ መእልክት አግኝተናል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው በላይ ወደ አሜሪካ መሰደዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።