ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኦነግ “የህወሀት ሽብር ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል አይገታውም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለአለፉት 11 ወራት መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ መቆየታቸውን አስታውሷል። ሙስሊሞች ያቀረቡት ጥያቄ፣ የይስሙላው ህገመንግስት እንኳን የሚፈቅደው ነው የሚለው ኦነግ፣ ሰሞኑን በገርባ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ግድያ ፣ ሌላው የህወሀት ጭካኔ ማሳያ ነው ብሎአል። አዲሱ የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር የህወሀትን የግድያ አጀንዳ በማስፈጸሙ ተጠያቂ እንደሚሆን ግንባሩ ጠቅሷል።
ኦነግ በገርባ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በጥብቅ እንደሚያወግዝ ጠቅሶ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አካባቢና ሀይማኖት ሳይገድበው ከሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
ኦነግ አለማቀፉ ማህበረሰብም በገርባ ህዝብ ላይ የተወሰደውን እርምጃ በማውገዝ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የግንባሩ ሊቀመንበር ጄ/ል ከማል ገልቹ የሙስሊሞችን ጥያቄ የሚደግፉት መንግስት እንደሚለው የሀይማኖት አክራሪነት እንዲስፋፋ ሳይሆን ሙስሊሙ የጠየቀው የመብት ጥያቄ በመሆኑ ነው ከኢሳት ጋር ባደረጉት አጭር ቃለምልልስ ገልጠዋል።
በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የመገንጠል ጥያቄውን በመተው ከኢትዮጵያ ሀይሎች ጋር በጋራ ለመታገል መወሰኑ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ ሉቅማውያን ኢትዮጵያውያን ቤልጂየማውያን ሙስሊሞች ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አብየ ያሲን በገርባ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ግድያ መንግስት በሙስሊሞች ላይ የሚያደርገውን አፈና አጠናክሮ ለመቀጠል የፈጠረው ነው ብለዋል
አቶ አብየ ንጹሀንን በጥይት እየቆሉ መግደል አሳዛዥ ቢሆንም፣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሰላማዊ እርምጃ ከመውሰድ ውች አማራጭ አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል
ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው የኢድ አል አደሀ በአል ላይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፍተኛ ተቃውሞ ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል። የሙስሊሙ ኮሚቴ አመራሮች ክስ ውድቅ እንደተደረገ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ቢዘገበም፣ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የወጡ ጽሁፎች እንዳመለከቱት ከሆነ ግን የኮሚቴ አመራሮች ክሳቸው ከአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ወደ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተዛውሯል።
በነገው እለት በሚኖረው ተቃውሞ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ምርጫው ” ህገወጥ ነው፣ ምርጫው የካድሬ ነው፣ ምርጫችን በመስጊዳችን፣ ኮሚቴው ይፈታ፣ ስቃዩ በቃን፣ ጭቆናው በቃን ፣ ውሸት በቃን፣ ህገመንግስቱ ይከበር” የሚሉ መፈክሮችን በመላው አገሪቱ እንደሚያሰሙ ከሙስሊሙ አስተባበሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ውድ ተመልካቾቻችን ስቱዲዮ ከገባን በሁዋላ በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ከኮሚቴ አመራር አባላት ጠበቃ ከሆኑት ከአቶ ተማም አባ ቡልጋ ጋር አጭር ቃለምልልስ አድረገናል።