ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ሽልመቷን ተቀበለች

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት ተከሳ በቃሊቲ እስር ቤት የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የ2012 የ ዓለማቀፍ የሴቶች ሚዲያ ፍውንዴሽን ሽልማትን ተቀበለች።

 

የኢትዮፎረሙ ዳዊት ከበደ እንደዘገበው  የጋዜጠኛ ርዕዮትን ሽልማት ኒዮርክ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ተገኝቶ  የተቀበለው የፀሀይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት ጋዘተጠኛ ኤልያስ ወንድሙ ነው።

——————–

ሽልማቱን ለመቀበል ቀደም ሲል የታጨው ጓደኛዋ ስለሺ ሃጎስ ቢሆንም፤ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ለመምጣት ቪዛ በመከልከሉ ምክንያት በስፍራው ሊገኝ አልቻለም።

በመሆኑም የ ኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች አለኝታ የሆነው የጸሃይ  አሳታሚ ድርጅት ጋዜጠኛ ኤልያስ ወንድሙ በስፍራው ተገኝቶ ሽልማቱን  ተቀብሏል።

 

በስነ-ስርዓቱ ላይ ጋዜጠኛ ርዕዮት ከቃሊቲ እስር ቤት የላከችው መልዕክትተነቧል።

የ አገር ጉዳይ ግድ እንደሚለውና ሀላፊነት እንደሚሰማው ጋዜጠኛ እየተፈጸሙ ያሉ ኢፍትሀዊ ድርጊቶችን በብዕር ከመንቀሷ ውጪ የተመሰረተባት ክስ እሷን እንደማይመለከታት የገለጸችው ርዕዮት፤ሀሳቧን በመግለጿ ምክንያት  ለእስር መዳረጓንና አሁንም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ማናቸውም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

ለ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ባስተላለፈችው መልዕክትም፦< ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ የ ኢትዮጵያ ቴሌቪንና የመንግስት ባለስልጣናት የሚነግሯችሁ ዓይነት አይደለችም። ትክክለኛው ኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ እንደኔ የታሰሩ ሰዎች የሞሉባት ናት። ይህን መጥፎ ሁኔታ ለመቀየር የቻላችሁትን ያህል ጥረት እንድታድርጉ እጠይቃለሁ>> ብላለች፡፤