ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፤ በአራት ቡድኖች ተከፍሎ በታላቅ ሽኩቻ ውስጥ ይገኛል ተባለ።
ፍኖተ ነጻነት ታማኝ ምንጮችን ጠቅሶ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፤ በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው “ኦህዴድ-መለስ” የሚባለው አንጃ ከህወሀት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ የአቶ መለስን ራእይ እውን ከማድረግ ውጪ የተለየ አመለካከቶችን ሁሉ የሚቃወም ነው።
አቶ ኩማ ደመቅሳ፤ አቶ ሙክታር ከድር፤ ወ/ሮ አስቴር ማሞና፤ አቶ ዘላለም ጀማነህን ያቀፈው “ኦህዴድ-ለመለስ” ቡድን፤ በኦህዴድ የተነሳውን የሰልጣን ይገባኛል ጥያቄ በጽኑ የሚቃወምና ሕወሀትን ለማገልገል ብቻ ታጥቆ የተነሳ መሆኑን ፍኖተ ነጻነት አስፍሯል።
በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራው 2ኛው የኦህዴድ ቡድን አባዱላ ገመዳን ወደኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነት ማምጣትን መሰረት ከማድረግ ውጪ፤ ከአቶ ኩማ ደመቅሳ ቡድን የተለየ አመለካከት የለውም ተብሏል።
ይህ የአባዱ ገመዳ ቡድን፤ በኦሮሞ ህዝብም ሆነ በኦህዴድ ስም የፌደራል ስልጣን መጠየቅ ፈጽሞ ከሀዲነት ነው ብሎ ያምናል ያለው የፍኖተ ነጻነት ዘገባ፤ ይህ ቡድን ከሕወሀት የሚወርድለትን መደብ መዝለቅን አላማው ያደረገ ነው ብሏል።
በዚህ ቡድን ውስጥ አባዱላ ገመዳና የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ እንደሚገኙበት ምንጮችን ጠቅሶ ፍኖተ ነጻነት ዘግቧል።
3ኛው የኦህዴድ ቡድን “ኦህዴድ ኦሮሚያ” የሚባል ሰያሜ ያለው ሲሆን፤ ይህ ቡድን ኦህዴድ ከሕወሀት ጥገኝነት ወጥቶ ኦሮሞንና ኦሮሚያን ማገልገል አለበት የሚል አላማ የያዘ ነው፤ እንደዘገባው ከሆነ።
ይህ ቡድን በአባልነት ወጣቱንና መካከለኛ እድሜ ያላቸውን ሰዎች ያሰባሰበ መሆኑ ሲገለጽ፤ የሕሀወት ተላላኪ ናቸው የሚላቸውን የአመራር አባላት ከድርጅቱ ማጥፋት የሚል አቋም አለው።
በኦህዴድ ውስጥ በ4ኛ ቡድንነት የተጠቀሰው “አድፍጥ ቡድን” የተባለው መሆኑን ይህ ሪፖርት የገለጸ ሲሆን፤ ይህ ቡድን አቋሙን በግልጽ ያሳወቀና ወደአሸናፊው ለመቀላቀል ያደፈጠ ነው ተብሏል።