በቶሮንቶ የኢሳት የድጋፍ ጽ/ቤት ተከፈተ

ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቶሮንቶና አካባቢው የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ ሥራውን በሚገባ ለማከናወንና ከህብረተሰቡ ጋር ሊያገናኘው የሚያስችል አዲስ የጽህፈት ቢሮ ትናንት ኦክቶበር 20, 2012 ከፈተ።

በ2017 –B2 Danforth Ave. የተከፈተው ይህ ጽህፈት ቤት የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ኢሳትን በዜናና በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ከማገዝ በተጨማሪ; በገንዘብና በሃሳብ የሚደግፉ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ለማስተባበር እንደሚጠቀምበት የኮሚቴው አባላት በምረቃው ስነስርዓት ላይ አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ አቅሙ በፈቀደው መጠን በተለያየ ቦታ በመሰብሰብ ለአካባቢው ህብረተሰብ የኢሳትን ተልዕኮ ለማስረዳትና ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን ገልጾ በቅርቡ በተደረገው የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም ያገኘውን 10,000 ብር ለኢሳት ማጠናከር ማረከቡን በማሳወቅ ድጋፍ ያደረገውን የቶሮንቶና አካባቢው ህብረተሰብ አመስግኗል።

በቢሮው የምረቃ ስነስርዓ ላይ እንዲገኙ ጥሪ የተደረገላቸው በቶሮንቶና ባካባቢው የሚገኙ ህዝባዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች በፖለቲካ፣ በዘርና በዕምነት ልዩነት ተከፋፍሎ  ሰላምታ እንኳ መለዋውጥ የከበደውን ህብረተሰብ በማገናኘትና ያልተዛባ መረጃ በመስጠት ኢሳት እየተወጣ ያለውን ከፍተኛ ሚና አድንቀው በሚፈለገው መንገድ ሁሉ ኢሳትን ለመርዳት ቃል ገብተዋል። ኢሳት በዜና አቀራረቡና በተለያዩ ዝግጅቶቹ የተወሰኑ ቡድኖችን ሆነ ግለሰቦችን አቋም ወደማንጸባረቅ ድክመት ውስጥ እንዳይገባ ከተሰብሳቢዎቹ አንዳንዶቹ ስጋታቸውን ሲገልጹ፤ ኢሳት በሰለጠነ የሰው ሃይል፣ በቁሳቁስና በልምድ መጎልበት፣ እንዲሁም የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ስጋቱን እንደሚያስወግድ የድጋፍ ኮሚቴው አባላት አስረድተው የኢሳት ወገንተኝነት ለእውነትና ለሃገር እንደሀኖነ አስረድተዋል።

ተሰብሳቢዎቹ ኢሳት በቶሮንቶ ዙርያና ብሎም ባጠቃላይ ካናዳ ማድረግ ስላለበት እንቅሳሴ ገንቢሃሳቦችን ከሰጡ በህዋላ ለውደፊቱም ኢሳት በሚኣደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከጎኑ ለመቆም ቃልገብተዋል።

ይህንን ዘገባ ከቶሮንቶ ያጠናቀረው፤ ጋዜጠና አንተነህ መርእድ ነው።