በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው

ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሊቢያ ቤንጋዚ በስደት የሚገኙ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን በስደተኞች ላይ በደል እየደረሰባቸው መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን ስደተኞች በካምፕ ውስጥ እና በእስር ቤቶች ክፍተኛ በደል እየደረሰባቸው መሆኑ ተገለጿል።

በቀይ ጨረቃ ካምፕ እና እስር ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሊቢያ ወታደሮች ድብደባና አስገድዶ መድፈር እየደረሰባቸውም ነው ተብሏል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁና ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ቃል የተመላለሱ በቤንጋዚ የሚገኙ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን በጋፉዳ እስር ቤት እና በቀይ ጨረቃ ካምፖች ከ1350 በላይ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን ይገኛሉ።

በአሁኑ ሰአት ምግብ እንኳ የሚያቀርብልን የለም ያሉት ኢትዮጲያውያን፤ በአከባቢው ያለው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ክፍተኛ ኮምሽን መጥተው የተለያየ ጥያቄ ጠይቀዋቸው ቢሄዱም፤ አንዳች ድጋፍ ሊያድርጉላቸው አልቻሉም።

በቀይ ጨረቃ ካምፕ ቤንጋዚ ቀድሞ ከ600 በላይ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን እንደነበሩ ያመለከቱት ስደተኞቹ ካምፑን እንዲጠብቁ በተመደቡ የሊቢያ ወታደሮች በሴቶቹ ላይ አስገድዶ መድፈር በወንዶቹ ላይ ድብደባ ማሰርና በከባድ ወታደራዊ ቅጣት ማሰቃየቱ ስለበዛ ከፊሉ ከካምፑ በመጥፋት ያሉበት አይታወቅም ብለዋል።

በጋፉዳ እስር ቤት ብቻ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን እንደሚገኙ የገለጹልን ምንጮቻቸን በእስር ቤቱ የሚፈጸምባቸው በደል ከካምፑ የባሰ መሆኑን በማመልከት የድረሱልን ጥሪ አስተላልፈዋል። በተለያየ ግዜ ወደ ስደተኛ ካምፑ ጋዜጠኞችና የበጎ አድራጊ ድርጅቶች መጥተው እንደጎበኟቸው የተናገሩት ስደተኞቹ ለነዚህ አካላት የሚደርስብንን በደልና ያለብንን ችግር የተናገሩ ክፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል ከፊሎቹም ወደ እስር ቤቶች ተዛውረዋል ሲሉ ገልጸዋል።