መስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አወዛጋቢ የሆነው የእስልምና ምክር ቤቶች ምርጫ የአብዛኛውን ህዝብ ድጋፍ ሊያገኝ እንዳልቻለ ነው ሙስሊሞች የሚናገሩት።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሙስሊሞች ለኢሳት እንደገለጡት መንግስት ህዝቡን በማስፈራራት በምርጫው በግድ እንዲሳተፉ እያስገደደ ነው። በጅማ ነዋሪ የሆነች አንድ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ወጣት “ህዝቡ በምርጫው የሚሳተፈው አምኖበት ሳይሆን ተገዶ ነው ” ትላለች
መንግስት በቀበሌ ቤቶች የሚኖሩትንም ሆነ ከቀበሌ የተለያዩ አገልግሎት የሚያገኙትን ሙስሊሞች እያስፋራራ መሆኑን ወጣቷ ትናገራለች።
በአሰላ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሙሀመድ አህመድ በበኩሉ በአሁኑ ጊዜ የቀበሌ ካድሬ ሌላውን ስራ ትቶ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ መግባቱን ገልጦ ፣ በቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በማስፈራራት በምርጫው እንዲመዘገቡ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም
“መንግስት የሙስሊሙን ምርጫ ብቻ ለይቶ በቀበሌ ውስጥ መካሄድ አለበት እንዳለ አይገባኝም የሚለው ወጣት ሙሀመድ፣ መንግስት ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ለማጋጨት የሚያደርገው ጥረት እንዳልተሳካለትም አክሏል
መንግስት ዋና አላማው አህባሽን ማምጣት ነው የሚለው ወጣት ሙሀመድ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊሞች እንዲፈቱም ጠይቋል
ሌላው በአዲስ ዘመን የሚኖረው ተማም ሻፊ በበኩሉ በአካባቢው የመንግስት ካድሬዎች ህዝቡ ለምርጫ እንዲወጣ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን አጋልጧል
በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገው ወጣት ደግሞ በነገውን ምርጫ ሊሳተፉ የሚችሉት የኢህአዴግ አባላት ወይም ተገደው የሚወጡት ብቻ ናቸው ተናግሯል
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ሽመልስ ከማል “ሙስሊሙ በምርጫው በነቂስ ወጥቶ መመዝገቡን፣ አብዛኛው ህዝብ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን ውድቅ ማደረጉን”ለብሉምበርግ ገልጠዋል።
በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ሙስሊሞች ከጁማ ጸሎት በሁዋላ ለመንግስት የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ መስጠታቸውን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide