በለገጣፎ እና በለገዳዲ አካባቢ የሚካሄደውን የመሬት ወረርሽኝን ለመገናኛ ብዙሀን ያጋለጡ ወጣቶች መታሰራቸውን ተከትሎ፣ የከተማው ነዋሪዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰሙ

መስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት እንደገለጡት ፣  የመንግስት ባለስልጣናትና ከእነርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ባለሀብቶች የሚያደርጉትን የመሬት ዝርፊያ  ለመገናኛ ብዙሀን ያጋለጡ ወጣቶች መታሰራቸውን ተከትሎ ከ500 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

 

መኮንን ተስፋየ፣ ጌታቸው ተፈራ፣ ድርባ ጉዳ፣ ገመቹ ወርቁ፣ እንዳልካቸው መንግስቱ፣ ምትኩ ንጉና ሲሳይ አለሙ የተባሉት ወጣቶች መረጃዎችን ለአሜሪካ እና ለጀርመን ድምጾች ሰጥታችሁዋል በሚል መታሰራቸው ታውቋል።

 

ቀደም ብሎ የአካባቢው ወጣቶች 900 የሚሆኑ ነዋሪዎችን ፊርማ በማሰባሰብ የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ነዋሪዎች አስታውሰዋል።

 

ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ የከተማው ከንቲባ የሆኑትን አቶ መገርሳ ገለታን ከወራት በፊት አነጋግሮ በዘገበበት ወቅት ከንቲባው ” ዬይዞታ ማረጋጋጫ ወረቅት ጠይቆ የተከለከለ የለም” የሚል መልስ መስጠታቸውንና ወጣቶችም ” እኛ ጠይቀን መች ተፈቀደልን” በሚል ምላሽ ጽፈው ለከንቲባውና ለመገናኛ ብዙሀን አስገብተዋል።

 

ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሀን መዘገቡ ያበሳጫቸው ባለስልጣናቱ ፣ ትናንት ከሌሊቱ 11፡ 30 ሰአት ላይ  የ7 ወጣቶችን ቤት በመፈተሽ ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል።

 

የአካባቢው ነዋሪዎች  ትናንት ወደ ፖሊስ ጣቢያው በመሄድ ወጣቶችን “ልቀቁዋቸው” ማለታቸው ታውቋል።  ከንቲባው ናዝሬት ለስብሰባ ሄደው በዛሬው እለት መመለሳቸውን መረጃ የደረሳቸው ወደ 500 የሚጠጉ ነዋሪዎች፣ ወደ መዘጋጃ ቤት በመሄድና በመክበብ ከንቲባው ወጣቶችን እንዲፈታቸው ጫና ሲፈጥሩ ውለዋል። የህዝቡ ተቃውሞ ያየለባቸው ከንቲባውም ወታቶቹ እንዲፈቱ ማዘዛቸውን፣  ፖሊስም ወጣቶችን ወደ በመውሰድ፣  የፊታችን ማክሰኞ ፍርድ ቤት እስከሚቀርቡ ድረስ በዛሬው እለት የዋስ መብታቸውን አስከብሮ ሊለቃቸው መዘጋጃቱ ታውቋል።

 

በለገጣፎና በለገደንቢ አካባቢ በሚካሄደው የመሬት ዝርፊያ ከፍተኛ የፌደራሉና የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት ይነገራል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide