ላኪዎች ንግድ ፈቃዳችንን ለመመለስ ተገደናል እያሉ ነው

መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-“መንግሥት ዘርፉን ከማሳደግ ይልቅ በየጊዜው የሚያቆረቁዙ አሠራሮችን እየተከተለ ነው” ያሉ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች፤ ንግድ ፈቃዳቸውን ለመመለስ እየተገደዱ መሆናቸውን ተናገሩ።

እንደ ነጋዴዎቹ ገለፃ መንግስት በዘርፉ እየተከተለ ያለው አሠራር አገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪም  እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።

ላኪ ነጋዴዎቹ  በመንግስት አሠራር ላይ ጠንካራ ተቃውሟቸውን ያሰሙት፤የአዲስ አበባ ንግድና ዘረርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ አካሂዶት በነበረው የጋራ የወጪ ንግድ ቡድን ስለመመሥረት አስፈላጊነት  ዙሪያ  በተካሄደ ውይይት ላይ ነው።

ነጋዴዎቹ ካነሷቸው ቅሬታዎች ውስጥ፣ የንግድ ሚኒስቴርና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን  እያስቀመጡ ለወጪ ንግዱ እንቅፋት እየፈጠሩ ናቸው የሚለው ይገኝበታል::

ጥቂት መጠን ያላቸውን ምርቶች ወደ ውጭ  በመላክ ተግባር ላይ የነበሩ ነጋዴዎች በበኩላቸው ፦<< መጋዘን ካልከፈታችሁ>>

እየተባሉ መቸገራቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ወደ ውጭ ለመላክ የሚዘጋጁ ኩባንያዎችም መንግሥትን ኮንነዋል::

ላኪዎቹ በየጊዜው የሚለዋወጡ ሕጎችና የመሥርያ ቤቶች   አሠራሮች ችግር  እንደፈጠሩባቸው ተናግረዋል።

መንግስት ፤የንግድ ሚኒስቴር ሥራዎች የነበሩ ጉዳዮች ወደ ሌላ መሥርያ ቤት እንዲዛወሩ  እያደረገ ሥራቸውን ያበላሸ አካሄድ  እየተከተለ መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎች፣ በተለይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በንግድ ሚኒስቴር መካከል የተከፋፈሉ ሥራዎች ለንግዱ ማኅበረሰብ ራስ ምታት መሆናቸውን በምሬት ገልጸዋል::

ሪፖርተር እንዳለው፦<<የኤክስፖርት ዕቃዎችን አንዴ ወደ ንግድ ሚኒስቴር፤ አንዴ ወደ ጤና ጥበቃ በማመላለስ ጭምር እየታወክን ነው>> ብለዋል-ነጋዴዎቹ::

በተለያዩ ዘርፎች የተጋረጡባቸውን ችግሮች ዋቢ እየጠቀሱ በዝርዝር ያቀረቡት ላኪዎቹ፤<< የንግድ ፈቃዳችንን ለመመለስ ዝግጅት ጀምረናል>> ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide