ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ስርጭት ለሦስተኛ ጊዜ ተቋረጠ።

ሐምሌ 19 ቀን 2002 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) በኢትዮጵያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮፓ አገሮች የሚያሰራጨው
የቴሌቪዥን አገልግሎት ከ ሀምሌ 19 ቀን 2002 ዓም ጀምሮ ለሦስተኛ ጊዜ ተቋርጦአል። በተመሳሳይ ጊዜም በኢትዮጵያ
መንግሥት የሚተላለፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭትም ከአገልግሎት ውጭ ሆኖአል።
ሥርጭቱ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲቋረጥ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን በእጃችን የሚገኙ
ማስረጃዎች አረጋግጠውልናል። ከ ሐምሌ 19 ቀን 2002 በፊት የኢሳት ስርጭት ባልተቋረጠ መልኩ የሳተላይት ሞገዶች
እየተለቀቁበት በተመሳሳይ ስርጭት ውስጥ የነበሩ ሌሎች ከ10 በላይ የሳተላይት ስርጭቶችም ይታወኩ ነበር። የሳተላይት
ስርጭቱን የሚሰጠው ኩባንያም ኢሳትንና በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰራጨውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲወርዱ
አድርጓል።
በኢሳት የተጠናቀሩት ማስረጃዎች የሚያሳዩት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንዳንድ በሳተላይት ንግድ ከተሰማሩ ድርጅቶች
ጋር በማበር የኢሳትን አገልግሎት ለማሰናከልና ብሎም ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው። ይኸው
የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊት የራሱን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎትን ጭምር አውኮታል።
ኢሳት በሥራው አግባብነት ካላቸው ከሌሎች አካሎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በእንደዚህ ልዩ መብት ባለው
ንብረት በሆነው በሳተላይት ኮሙኒኬሽን ሥራ ላይ የሚፈጽመውን የሕገ-ወጥ ተግባር እንዲያቆም ለማድረግ ሕጋዊ
ሁኔታዎችን በመመርመር ላይ ይገኛል።
ኢሳት ከተጠቃሚው ከኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሰጠው ድጋፍና ማነቃቀያ እየታገዘ ዜናዎችን፣ መረጃዎችንና የመዝናኛ
ዝግጅቶችን የማቅረብ ተልእኮውን ይቀጥላል። ከዚህ ቀደም የኢሳት ሥርጭት ሲታወክ እንዳደረግነው ሁሉ ዛሬም
ለደጋፊዎቻችን ያለንን አድናቆት እንገልጻለን።
በተለይም ለደጋፊዎቻችንና ለተመልካቾቻን ለማረጋገጥ የምንወደው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሥርጭታችን ላይ
የቀጠለውን የማወክ ሥራ ለማቆም ሕጋዊና ቴክኖሎጅካዊ መንገዶችን ሁሉ ለመጠቀም ጥረት በመድረግ ላይ
መገኘታችንን ነው። በመሆኑም፣ ደጋፊዎቻችንና ተመልካቾቻን የኢሳት ሥርጭትን ለመቀጠል የምናደርገውን ትግል
በትዕግሥት እና በጽናት መከታተልና መደገፍ እንድትቀጥሉ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

የኢሳት አስተዳደር
ስልክ 0031 20 33 17 176
አምስተርዳም