የኢሳትን ወደ ዓየር መመለስ በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣

ኀዳር 23፣ 2003 ዓም
በጋራ ጥረት የኢሳትን ህልውናን ማረጋገጥ፣
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ነጻን ሚዛናዊ የመገናኛ ብዙሀን ተቋም መሆኑን፣ በኢዲቶሪያል ፖሊሲው ያስቀመጠው ብቻ ሳይሆን፣
ሥራ ከጀመረበት ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በተግባር ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። ለዚህም ጠንካራ መረጃዎቹ በየጊዜው ያስተላለፋቸውና
ዛሬም እያስተላለፋቸው ያሉት ፕሮግራሞቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ሥር በሆኑባቸው ሐገራት
ሊኖረው የሚችለው ትርጉም ምን ያህል እንደሆነ፣ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እያስተላለፍን በነበረ ጊዜ በህዝቡ ዘንድ የቀሰቀሰውን የነጻነት
ተስፋ፣ በቃላት ለመግለጽ ያስቸግረናል። ለዚህም ነው፣ ኢትዮጵያ በቀጥታ እንዳይተላለፍ በየጊዜው ችግር እየፈጠረብን ያለው አካል፣
በሕዝብ የነጻነት ተስፋ መቀስቀስ ስጋት ላይ የወደቀው በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው የመንግስት መሆኑንን በበቂ መረጃዎች
ለማረጋገጥ የቻልነው። ምንም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ የምናስተላልፈው ፕሮግራም ከተቋረጠ ስድስት ወራቶች ቢያስቆጥርም፣ በነዚህ
ወራቶች ውስጥ ወደ ዓየር ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች ስናደርግ ቆይተናል።
በዛሬው ዕለትም ወደ ዓየር መመለሳችን የዚህ ከፍተኛ ጥረታችን ውጤት ነው። ካለፈው ልምዳችን እምደምናውቀው ወደ ዓየር
መመለሳችን ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መልካም ዜና የመሆኑን ያህል፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ግን በቀና እንዳማያዬው እና
የለመደውን የተንኮል እርምጃ መውሰዱ የማይቀር መሆኑን ነው። እኛ ግን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ የምንፈልገው ጉዳይ ቢኖር፣ ነጻና
ሚዛናዊ መረጃ ማግኘት ሰብዓዊ መብታችን ስለሆነ፣ ይህንን የእኛን እና የወገናችንን መብት ለማስከበር ዛሬም ነገም ምንም ዓይነት ዋጋ
ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን ነው።
ወደ ዓየር ለመመለስ ከአደረግነው ያላሰለሰ ሙከራ በተጓዳኝ፣ የፕሮራሞቻችንን ብዛትና ጥራት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ
እንገኛለን። በአሁኑ ጊዜ ዋናውን ስትዲዮያችንን በሁለገብ አገልግሎት ሊረዱ የሚችሉ በለንደን የፕሮዳክሽን ቡድን አቋቁመን ሥራ
የጀመረ ሲሆን፣ በዋሽንግተን የተጨማሪ ስቱዲዮ ሥራ በመጠናቀቁ ወደ ፕሮግራም ምርት መግባት ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ
በኢንተርኔት የሃያ አራት ሰዓት አግልግሎት ለተወሰነ ዚዜ በነጻ እየሰጠን ነው።
በዚህ አገልግሎት ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ ከሌላ የዜና ምንጮች የማይገኙ ዜናዎች እና ሌሎች ፕሮግራሞች ለተመልካች ማቅረብ
ችለናል። ይህንን አገልግሎት ወደፊትም በተሻለ ጥራትና ስፋት ማስተላለፋችንን እንቀጥላለን። በአጠቃላይ ኢሳት የተሻለ ፕሮግራሞችን
የማቅረብ ዋስትና የሆነውን የማናቸውም ዓይነት ፕሮግራም የመሥራት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደግን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
በመጨረሻም በሐገር ውስጥም ይሁን በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፣ ስለ ሐገራችን ሆነ ስለሌላው የዓለም፣ ሚዛናዊና ነጻ መረጃ
ማግኘት ሰብዓዊ መብታችን ነው። ይህን መብታችንን የማስከበሩ ጉዳይ የሁላችንም በመሆኑ፣ በምትችሉት፣ በሰብስክሪፕሽን
የኢንተርኔት አገልግሎታችንን በመከራየት፣ ቀጥታ የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የሞራል እርዳታ በማድረግ ኢሳትን እንድትረዱን ጥሪያችንን
እናቀርባለን።
አዲሱ የስርጭት መረጃ፣
Thaicom5 Satellite, C-Band at 78.5E, Transponder:6G, Downlink:3640H, Symbol:28066, FEC 3/4
ሁላችንም በጋራ በምናደረገው ጥረት የኢሳት ህልውና ይረጋገጣል!!!
ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ፣
www.ethsat.com