በትናንትናው እለት የኢራን መንግስት ዋና ከተማዋ ቴህራን ቦታዎች ላይ አድማ በታኝ ፖሊስ እንዳሰማራ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ

መስከረም ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፖሊስ የተሰማራው በሀገሪቱ ላይ የተደረጉ ማእቀቦች በኢኮኖሚው ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ተጽእኖ መኖር ከየአቅጣጫው የህዝብ ተቃውሞ በመፈጠሩ ነው።

በተለያዩ ቦታዎች በተደረገው ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር በተደረገው ግጭት የቆሻሻ መጣያ ገንዳዎች በእሳት መያያዘችው ተዘግቧል።

በቴህራን ዋና መገበያያ ቦታ ላይ ቀደም ባሉት የስራ ቀናት ተዘግተው የቆዩት በርካታ የንግድ ቤቶች ሀሙስ እለት ቢከፈቱም፤ በሁሉም ስፍራ አለመረጋጋት እንዳለ ተዘግቧል።

መንግስት ሕገወጥ ያላቸውን የውች ምንዛሬ ነጋዴዎች ማሰሩን አስታውቋል። እነዚህ ነጋዴዎች የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ተጽእኖ እንዳሳደሩ ይታመናል።

የመንግሥት ዐቃቤ ሕግ፤ የኢራን ገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል አጋጣሚ በመጠቀም፤ “የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በማናወጥ”፤ በሚል በቴሕራን 16 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።

የኢራን መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2009 በተደረገው አወዛጋቢው የፕሬዚዳንት ማሕሙድ አህመዲነጃድ ዳግም ምርጫ ላይ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ በጉልበት ካከሸፉበት ጊዜ ወዲህ የተከሰተው ተቃውሞ ባለሥልጣኖችን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ጥሎአቸዋል ተብሏል።

የነጋዴዎች ማኅበር ዋናው የችግሩ መንስኤ የመንግሥት የኢኮኖሚ አያያዝ መሆኑን ጠቅሰው ፖሊስ በቴህራን ገበያ ለሚገኙ ሱቆች ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአህመዲነጃድ መንግሥት ባንኮች ወለድን እንዲገድቡ የሚያደርግ ፖሊሲ በማውጣታቸው ምክንያት ዜጎች ዋጋ ያጣል በሚል ፍርሃት ገንዘባቸውን ከባንክ ማውጣታቸው ለኢኮኖሚው ቀውስ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ተቺዎች ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሂላሪ ሮድሃም ክሊንተን፣ ኢራን አሁን ላለችበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የመሪዎቹ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሴኩሪቲ ካውንስል ኢራን የኑክሊየር ፕሮግራሟን የጦር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችል ብቃት እየገነባችበት ነው በሚል እ.ኤ.አ. ከጁላይ 2006 ጀምሮ በየጊዜው ማዕቀብ መጣሉና ማእቀቡን እያጠነከረ መምጣቱ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide