መስከረም ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልልሎች የጎዳና ላይ ሩጫ ለተለያዩ ዓላማዎች በማካሄድ ያገኘው ሀብት ሕገወጥና ከተመሠረተበት ዓላማ ውጪ ነው ተብሎ ሊወረስ መሆኑን ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ
ከ12 አመታት በላይ በየዓመቱ በአዲስ አበባ ላይ የ10 ሺሕ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በማካሄድ እውቅና ያገኘው የአትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ድርጅት ፣ የበጎ አድራጎት ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ ተሰጥቶት እያለ ከተመዘገበበት ዓላማ ውጪ በአትራፊ ድርጅትነት ሲንቀሳቀስ መገኘቱንና ከዚህም መንግሥት ተገቢውን ጥቅም አላገኘም በሚል ነው እንዲወረስ የሚደረገው።
እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር 2012 መጨረሻ ድረስ አሁን ያለው ሕጋዊ ሰውነት የሚጠበቅለት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን ከኤጀንሲው መዝገብ እንደሚሰረዝና ሀብትና ንብረቱም ተወርሶ በሕጉ መሠረት እንደሚስተናገድ የመንግስት ባለስልጣናት ለጋዜጣው አስታውቀዋል፡፡
ድርጅቱ በባንክ ያለው ገንዘብ ተጣርቶ አሥር ሚሊዮን ብር እንዳለው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሌሎች ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶችም ተመዝግበዋል ። አትሌት ሀይሌ እኤአ እስከ ዲሰምበር 2012 ድረስ የሚያገኘውን ሌሎች ገቢዎች ጨምሮ ለኤጀንሲው እንዲያስረክብ ታዟል።
አትሌቱ እስከተባለው ቀን ድረስ የታላቁን ሩጫ ንብረት ባያስረክብ ኤጀንሲው ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ የመንግስት ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል። አትሌት ሀይሌ ከስፖርት ኮሚሽንና ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ታላቁን ሩጫ ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱን ገልጦ፣ የታላቁ ሩጫን ሀብትና ንብረትን በተመለከተ ግን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቋል።
“አንድ ቀን ስፖንሰሮችን ብናጣ ሩጫው መቋረጥ የለበትም በሚል እሳቤ ያስቀመጥነው ሀብትና ንብረት አለ፤ ይህ ሀብት ተወርሶ ታላቁ ሩጫን ማስቀጠል አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ የለፋንበትን ታላቁ ሩጫን በገንዘብ እንደመግዛት ይሆንብኛል፤” ሲል ይህ እንዳይከሰትና ታላቁ ሩጫ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ኃይሌ ምኞቱን ገልጿል፡፡
አትሌት ሀይሌ ለገዢው ፓርቲ በሚያሳየው ድጋፍ በተቃዋሚዎች ዘንድ በተደጋጋሚ እንዲተች አድርጎታል። አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ አትሌት ሀይሌ እንባ እየተናነቀው፣ “ጀግናው አልሞተም ” በማለት ሀዘኑን ሀዘኑን ሲገልጥ እንደነበር ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide