የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኮበለሉ

መስከረም ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአሁኑ ወቅት በኃላፊነት ላይ ባለው የኩማ አስተዳደር የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ያገለገሉትና ከአንድ ዓመት በፊት በአቅም ማነስ ተተችተው ከኃላፊነታቸው የተነሱት አቶ ከፍያለው አዘዘ ወደ ዩናይትድስቴትስ አሜሪካ ቤተሰባቸውን ይዘው መኮብለላቸው ተሰማ፡፡

አቶ ከፍያለው ከ1997 ዓ.ም ምርጫ አለመግባባት ጋር በተያያዘ በገዥው ፓርቲ ተሹሞ የነበረውን የባለአደራውን የአቶ ብርሃነ ደሬሳ አስተዳደር በግንቦት ወር 2000 ዓ.ም በይስሙላ ምርጫ በተካው የአቶ ኩማ ደመቅሳ ካቢኔ ውስጥ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሥራአስኪያጅነት ኃላፊነታቸው በመነሳት በቀጥታ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ለመሾም
ችለው  ነበር፡፡

አቶ ከፍያለው በተሾሙበት ወቅት ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚያበቃ ልምድ የላቸውም በሚል በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ቢተቹም ገዥው ፓርቲ ግን አስተያየቱን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ሆኖም ከአንድ ዓመት በፊት “እስከቀበሌ ባሉ መዋቅሮች ጭምር የራሱን ቡድን አደራጅቷል፣የአቅም ችግርም አለበት” በሚል ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በመሩት ግምገማ ተብጠልጥለው ከሥልጣናቸው ተሰናብተዋል፡፡

አቶ ከፍያለው ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኃላ የአቶ ኩማ አማካሪ ተብለው መቀመጣቸው በይበልጥ ሞራላቸውን የነካ ጉዳይ እንደነበር ምንጮቻችን አስታውሰዋል፡፡

አቶ ከፍያለው ከ15 ቀናት በፊት ለዕረፍት በሚል በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑ ባለቤታቸውንና ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ ማቅናታቸውንና ላለመመለስ መወሰናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ከፍያለው አዘዘ በኢትዮጰያ ራዲዮ ጋዜጠኛ የነበሩ ሲሆን ብአዴንን ከተቀላቀሉ በኃላ በፕሬስ መምሪያ ኃላፊነትና ሥራአስኪያጅነት ተሹመው ለረዥም ጊዜ አገልግለዋል፡፡

ከአመት በፊት የማስታወቂያ ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት  አቶ ኤርምያስ ለገሰ አገር ጥለው መኮብለላቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብአዴን ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ባደረገው ስብሰባ ፣ የአቶ ሀይለማርያም እና የአቶ ደመቀ መኮንን ሹመት ለድርጅቱ ትልቅ ድል መሆኑን ለአባሎቹ ገልጧል። ብአዴን ላላፉት 20 አመታት የህወሀት ጅራት ነው እየተባለ ሲተች መቆየቱን ያስታወሱት የድርጅቱ አባሎች፣ በአዲሱ አመራር ድርጅታቸው የህወሀትን የበላይነት በማስቀረት ድርጅታቸው የተጫወተውን ሚና ሲያደንቁ መሰማታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጠዋል።

የብአዴን አመራሮችም የስልጣን ሽግግሩን በኩራት ለአባሎቻቸው ሲገልጹ እንደነበር ታውቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide