የአሜሪካ መንግስት የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ታሪካዊ ነው አለ

መስከረም ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ የታየው የስልጣን ሽግግር ታሪካዊ፣ ሰላማዊና ህገመንግስታ ነው በማለት አወድሶታል።

አሜሪካ ከአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መመሰርቷን የገለጠው መግለጫ ፣ በሚቀጥሉት አመታት የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ለማጠንከር፣ ሰብአዊ መብቶችንና ዲሞክራሲን ለማጎልበት እንዲሁም የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ከእርሳቸው ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስተዳደሩ ገልጧል።

የአሜሪካ መንግስት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲመረጡ ግፊት ማድረጓን የተለያዩ ድረገጾች መዘገባቸው ይታወሳል። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቶ ሀይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ስልክ ደውለው አነጋግረዋቸው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

የኦባማ አስተዳዳር በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ በቂ ግፊት ባለማሳደሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዳይዳብር ና የሰብአዊ መብቶች እንዳይከበሩ ምክንያት ሆኗል በማለት ይተቻል።

በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌና ሌሎችንም የህሊና እስረኞች የኦባማ አስተዳዳር ለማስፈታት ያደረገው ጥረት አለመኖር፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን በኦባማ አስተዳዳር ላይ ያላቸውን ነቀፌታ ይሰነዝራሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide