(Sept. 10) በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጪ ግንባር (ኦብነግ) እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ድረድር እየተካሄደ መሆኑን፤ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጪ ግንባር የኢትዮጵያ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት ገለጡ።
አቶ ሀሰን አብዱላሂ እንደተናገሩት ድርድሩ በናይሮቢ በኬንያ መንግስት አደራዳሪነት ባለፈው ሀሙስና አርብ ተካሄዷል።
የኦጋዴን ነጻአውጪ ግንባር ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚደራደረው በሶስተኛ አገሮች መሆን እንዳለበት ጠይቆ የነበረ ሲሆን፤ ያንን ቅድመሁኔታ ሳይቀበል የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ባለፈው ሳምንት ቅድመ ሁኔታውን ተቀብሎ ድርድሩ በኬንያ መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል።
ከኦብነግ አቶ አብዱራህማን ማህዲ፤ ከኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፤ በአደራዳሪነት የኬንያው የእርሻና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በተገኙበት በዚህ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ላይ ምንም አይነት መሰረታዊ ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ፤ ነግር ግን የሌላ ዙር የድርድር ቀጠሮ ተይዞ ውይይቱ ባለፈው አርብ እንደተጠናቀቀ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ድርድር ላይ ለቀጣዩ ዙር ድርድር አጀንዳ እንደተያዘና የድርድር ቦታው እንደተወሰነም አቶ ሀሰን ገልጸዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢሳት በሁለቱ ወገኖች መካከል ድርድር ሊካሄድ እንደሆነ ዘግቦ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ አቶ ሀሰን አብዱላሂ የኢትዮጵያ መንግስት የሶስተኛ ወገን አደራዳሪነትን ባለመቀበሉ ምክንያት ድርድሩ እንዳልተደረገ ገልጸው ነበር።
በ1996 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግስት ለድርድር የመጡትን የኦብነግ ልኡካን በሙሉ እንደገደላቸውና በዚሀም ምክንያት በተደራዳሪዎቻችን ላኢ ተመሳሳይ እጣ ልደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለን ያለው ኦብነግ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድመሁኔታውን በመቀበሉ ድርድሩ በኬንያ ናይሮቢ እንደተካሄደና አሁንም በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት እንደሚቀጥል ታውቋል።