የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እንዳይታተም ታገደ

ነሀሴ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ሀሙስ እለት ተጨማሪ ልዩ ህትመታቸውን በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለማሳተም የ18 እሺ ጋዜጣ ዋጋ ለመክፈል የሄዱት የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ አዘጋጆች በማተሚያ ቤቱ ሁለተኛ ለእናንተ ጋዜጣ ህትመት በእኛ ማተሚያ ቤት አይታተምም ብለው እንደከለከሉዋቸው ታውቋል።

የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች የማተሚያ ቤቱን ሀላፊዎች ያነጋገሩ ሲሆን፣ ፣ እናንተ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሞት ለፕሮፓጋንዳ እና በሀዘን ጊዜ የማይደረግ ዘገባ ሰርታችሁዋል ስለዚህ እንኳን ልዩ እትም ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ይቅርና ሳምታዊ ህትመታችሁን ለማሳተም አንፈቅድላችሁም ተብለው ተመልሰዋል።

ፍትህ ጋዜጣ ከወር በፊት አቶ መለስ ስለመሞታቸው ከተለያዩ ወገኖች የተጠናቀረን መረጃ ለመዘገብ በመዘጋጀቱ  የጋዜጣው ሕትመት ጠቅላላውኑ  እንዲቆም መደረጉ  ይታወቃል።

በስላቅ ጽሁፉ የሚታወቀው ጋዜጠኛ አቤ ቶክቻው፦”ፍትሕ ጋዜጣ የ አቶ መለስን ሞት ለመዘገብ ሞክረሀል”ተብሎ እንዲቃጠል እና እንዲታገድ ከተደረገ፤ ቁርሳችንን ሳንበላ በጧቱ ስለ አቶ መለስ መሞት መርዶ የነገረን ኢቲቪ ምን ዓይነት ከባድ እርምጃ ይጠብቀው ይሆን?” ሲል መጠየቁ አይዘነጋም።

እንደ ፍትህ ጋዜጣ ሁሉ ፍኖተ-ነፃነትም ታግዶ የሚቀር ከሆነ፤ በኢትዮጵያ በመንግስት ላይ  ትችት የሚያቀርብ አንድም  ጋዜጣ አይኖርም ማለት ነው።

ኢሳት የ አቶ መለስን ሞት የዘገበው ከወር በፊት መሆኑን ያስታወሱ አስተያዬት ሰጪዎች፦” ፍትሕም ሆነ ፍኖተ-ነፃነት የታገዱት አቶ መለስ መሞታቸውን ተከትሎ ነው፤ ይህም ሚያሳዬው ሀቅ በ አቶ መለስ ምትክ ወደ ሥልጣን እየመጣ ያለው ቡድን ከበፊቱ በከፋ ሁኔታ ምን ያህል አፋኝና አምባገነን መሆኑን ነው”ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide