ነሀሴ ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የአዲስ አበባ አስተዳደር የጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት ጋር በተያያዘ በዕጣ የለያቸውን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለዕድለኞችን ዝርዝር “አዲስ ልሳን” የያዘውን ጋዜጣ “አገሪቱ ሐዘን ላይ ናት” በሚል ለሕዝብ እንዳይሰራጭ አገደ፡፡
ነሃሴ 13 ቀን 2004 ዓ.ም በሕዝብ ፊት በአዲስአበባ ማዘጋጃ ቤት ለ7 ሺ 300 የኮንዶሚኒየም ዕድለኞች ዕጣ የወጣ ሲሆን ዕድለኞች የዕጣውን ውጤት ከአዲስአበባ አስተዳደር ድረገጽ መመልከት ወይም የአስተዳደሩ ልሳን በሆነው
“አዲስልሳን” በተባለ ጋዜጣ ላይ ሲወጣ ጠብቀው መመልከትና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ እንዲያሟሉ ተጠይቀው ነበር፡፡
ሆኖም የጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት ነሐሴ 15 ቀን በይፋ መነገሩን ተከትሎ ነሐሴ 19 ቀን 2004 ዓ.ም የታተመውና የኮንዶሚኒየም ባለዕድለኞችን ዕጣ የያዘው ጋዜጣ ከቀብር በፊት ለሕዝብ እንዳይሰራጭ በመወሰኑ ሕትመቱ ወደመጋዘን እንዲገባ ተደርጎአል፡፡ በአስተዳደሩ ድረ ገጽ ላይም “በቅርብ ቀን ይጠብቁ” የሚል መረጃ በማስቀመጥ ዕጣው ይፋ ሳይሆን ቀርቶአል፡፡
ምንጫችን አስተዳደሩ ይህን እርምጃ የወሰደው በአ/አ ከተማ ከ300ሺ በላይ ሕዝብ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቦ ዕጣ የሚጠባበቅ በመሆኑ ዕጣው ይፋ ቢደረግ የጠ/ሚኒስትሩ ሞት የሕዝብ ትኩረት ሊያጣ ይችላል ከሚል ሥጋት የተነሳ መሆኑን ጠቁሞአል፡፡
ነሐሴ 13 ቀን 2004 ዕጣቸው የወጣው ቤቶች አስተዳደሩ በልደታ መልሶ ማልማት እና በሌሎች ነባር ሳይቶች የገነባቸውን 7ሺ300 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ ቤቶቹ የተገቡት በልደታ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ አዲስ ከተማ፣ ቂርቆስና የካ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide