እየታየ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕልፈት የሐዘን አገላለጽ አቅጣጫውን የሳተ እንዳይሆን፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መጠየቁን ሪፖርተር ዘገበ፡፡

ነሀሴ ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ እየታየ ያለው የሐዘን አገላለጽ ዓላማውንና አቅጣጫውን የሳተ እንዳይሆን፣ ሕዝቡም ሆነ የመንግሥት አካላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መጠየቁን ሪፖርተር ዘገበ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕይወታቸው ማለፉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ከተነገረ  ካለፈው ነሐሴ 15  ቀን  ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸው፣ በሁሉም ክልሎች እና ወረዳዎች  ሕዝቡ ሐዘኑን እየገለጸ መሆኑን የተናገሩ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፣ ዜጐች ሐዘን መድረስ ያለባቸው በእውነተኛ ሐዘን ላይ ተመሥተው እንጂ በጉትጐታና በቅስቀሳ መሆን እንደሌለበት መምከራቸውን ፤የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል።

በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ሕዝቡ በየአደባባዩ አለያም በየወረዳውና በየመሥሪያ ቤቶች በመገኘት ሐዘኑን እንዲገልጽ ደብዳቤና ቅስቀሳ ማካሄድ አግባብ እንዳልሆነ  ለጋዜጣው የገለጹት አስተያዬት ሰጪዎች፣ ሰሞኑን በየድረ ገጹ የወጡትን “ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ” አዘል ትዕዛዞችን  አውግዘዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈተ- ዜና ማክሰኞ ነሐሴ 15 ቀን  ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አማካይነት ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ፣ አስከሬናቸው ወደ አዲስ አበባ እስከገባበት ሰዓት ድረስ  በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን ሁኔታ ማንሳት በቂ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰዋል፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕይወት ማለፍ፤ አብዛኞቹን ኢትዮጵያውያንን፣ አፍሪካዊያንን፣ ከእሳቸው ጋር ቀረቤታ የነበራቸውን የዓለም መሪዎችንና አንዳንድ ወዳጆቻቸውን ማሳዘኑ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም፣ የተወሰኑትን ደግሞ ሊያስደስታቸው ይችላል  ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ዜጎች ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማቸውን ሐዘን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በተለይ በቴሌቪዥን የሚገልጹበት ሁኔታ -ለአላስፈላጊ ትችት የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ እየተስተዋለና እየተመረጠ የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲኖርም ጠቁመዋል-ብሏል-ሪፖርተር።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ፤ በሀዘኑ ሥርዓት  ሳቢያ ኢትዮጵያውያን ተረጋግተው  ሥራቸውን መሥራት አልቻሉም።

በመሆኑም   ከሀዘኑ  ጐን ለጐን ሥራዎቻቸውንም መሥራት እንደሚገባቸው  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክተው አገሪቱን እየመሩ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት መምከር  እንዳለባቸው የጠቆሙት የጋዜጣው አስተያዬት ሰጪዎች፤  ከዚያም አልፎ አንዳንዶቹን ግዙፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንና ፕሮጀክቶችን ጭምር በመጐብኘት ማበረታታት አለባቸው ብለዋል።

እንዲሁም ክፍላተ ከተሞቹም ሆኑ ወረዳዎቹ ግብር የመሰብሰብ ሥራቸውን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ማከናወን ሲገባቸው በዚሁ ምክንያት  ማቆማቸው የሚያስከትለው  ጉዳት አሁን ባይታወቅም ፤ጉዳዩ ሊተኮርበት  እንደሚገባ አሣስበዋል።
አስተያዬት ሰጪዎቹ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም ፦አመራሩ የደብዳቤ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ከልቡ ያልሆነውን ሁሉ፦” ወጥተህ ሐዘንህን ግለጽ” ከማለት እንዲቆጠብ ማሣሰባቸውን፤ የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።

በመላ አገሪቱ የተለያዩ ወረዳ ነዋሪዎች፣ልዬ ልዩ መስሪያ ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣የሙያ ማህበራት፣የትራንስፖርት ድርጅቶች  አትሌቶች፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች እና ሌሎችም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች  ለለቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ሀዘናቸውን ወደ ተዘጋጀው ሥፍራ እየወጡ እንዲገልጹ፤ የማሣሰቢያና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እየተሰራጨ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሦስት ቀናት በፊት ፦”ጎዳና ተዳዳሪዎች በአቶ መለስ ሞት የተሰማቸውን መሪር ሀዘን ገለጹ”በሚል ርዕስ ባስተላለፈው ዜና ላይ አንድ ጎዳና ተዳዳሪ፦”መለስ አባታችን፣አንተን ተማምነን እኮ ነው ጎዳና ላይ የምናድረው፤ አሁን አባት ሌለው ልጅ ሆነናል”እያለ ሲናገር መታየቱ፤ከማሳዘን አልፎ ብዙዎችን ፈገግ ያደረገ ሆኖ አልፏል።

በኑሮ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ የሚገኙት፣ ያለፉት 21 ዓመታት አገዛዝ ፍሬ የሆኑትና  ምግባቸውን ሳይቀር ከውሻ ጋር እየተሻሙ የሚበሉት እነዚህ አሳዛኝ ወገኖች፤  በአቶ መለስ ሞት ምን ቀረባቸው?ብለን እንድናስብ ነው ኢቲቪ ይሄን ውሀ የማይቋጥር ፕሮፓጋንዳ ያሳየን?ሲሉ  በአግራሞት ጠይቃዋል- የኢቲቪን ዜና የተመለከቱ ሰዎች;

ጎዳና ተዳዳሪዎቹ በሰልፍ ሀዘናቸውን ሊገልፁ መጡ በተባለ ጊዜ  በቤተመንግስት ውስጥ ሆኖ የሀዘኑን ሥርዓት ሲከታተል የነበረው  የኢሳት ወኪል  ሰልፋቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ከነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል ሁለቱን እንዴት ሀዘናቸውን ለመግለጽ ወደ ቤተ-መንግስት እንደመጡ ለብቻቸው ነጥሎ አነጋግሯቸው ነበር።

“ወደ ቤተመንግስት ሄዳችሁ ሀዘናችሁን ከገለፃችሁ በሁዋላ ዳቦ እና ለስላሳ መጠጦች ይሰጣችሁዋል ተብለን ቃል ስለተገባልን፤በዚያ ላይም ቤተመንግስትን ማየት ስለፈለግን  ልመናችንን አቋርተን መጥተናል” ብለዋል።

ከዚያም በማግስቱ ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ይዘው እየታከሙ ያሉ ህሙማን፦”ሀዘናችሁን ግለጹ”ተብለው  ህክምናቸውን አቋርጠው ወደ ቤተ-መንግስት ሲሄዱ መታየታቸው አይዘነጋም።

የአቶ መለስ የቀብር ሥነ ስርዓት  እንደ አገር መሪነታቸው በተገቢው ክብር መከናወን እንዳለበት እናምናለን የሚሉት አስተያዬት ሰጪዎች፤አሁን እየታዬ ያለው የተንዛዛ ነገር ሀዘኑን ወደ ቀልድ እየቀየረው መጥቷል ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide