9 ፓርቲዎች የጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ በመጪው እሁድ ሊካሄድ ነው

መጋቢት ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት የተሰባሰቡትና ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አልሰጠሁም በሚል ትብብራቸውን እንዲያቆሙ

ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ዘጠኝ ፓርቲዎች በትብብር የጠሩት ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የፊታችን እሁድ የአዲስአበባ እና የድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ በአስራአምስት ዋና ዋና ከተሞች ይካሄዳል፡፡

ሆኖም አዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከወዲሁ ሰልፉ በመንግስት በኩል ያልተፈቀደ ነው በሚል ለማጨናገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በባህርዳር መጋቢት 20 ሊካሄድ የታቀደው ሰልፍ እንደማይካሄድ መስተዳድሩ ደብዳቤ ጽፏል። በደብዳቤው ላይ እንደተመለከተው ሰልፉ በከተማዋ በመካሄድ ላይ ባለው አገራቀፍ የስፖርት ውድድርና በእለቱ የአባይ ቦንድ ግዢ ዝግጅት በመኖሩ ነው።

የምእራብ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ የሰልፉ ጊዜያዊ አስተባባሪ ወጣት አዲሱ ጌታነህ  እንደሚለው በምርጫ ወቅት ምንም አይነት ውድድር ቢኖር ቅድሚያ ለምርጫ ዝግጅቶች እንደሚሰጥ ገልጾ፣ ሰልፉ የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ከሚካሄድበት

ስታዲየም ራቅ ባለ ቦታ በመሆኑና ለተማሪዎች ውድድር የጸይታ ሃይሎች አስፈላጊነት አናሳ በመሆኑ፣ መስተዳድሩ ሰልፉን ሆን ብሎ መከልከሉን ተናግሯል።

ገዢው ፓርቲ ሰልፉን ለመከልከል የፈለገበት ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን ተብሎ ለተጠየቀው ደግሞ ” ህዝቡ በስርአቱ ላይ ሊያሰማ የሚችለው ተቃውሞ ገዢውን ፓርቲ ስጋት ላይ ስለጣለው ነው በማለት መልሷል

የሰልፉ ዋና አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ እንደተናገ  ሩት እስካሁን ድረስ ከአዲስ አበባም ሆነ ከሌሎች አካባቢዎች ሰልፉ እንዳይካሄድ የሚያግድ ደብዳቤ አለመቅረቡን ገልጸው፣ ሰልፎቹ በ15 ከተሞች በታቀደላቸው መሰረት ይካሄዳሉ ብለዋል።

አቶ ግርማ እንደሚሉት በምርጫ ቅስቀሳ ወቀት መስተዳድሮች የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያካሂዱዋቸውን ሰልፎች መከልከል እንደማይችልና ሰልፎቹ በማንኛውም መንገድ እንደሚካሄዱ ገልጸዋል

«ነጻነት ለፍትሐዊ ምርጫ» በሚል የታሰበው ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ የሚካሄድ ከሆነ በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ድጋፉን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የአዲስ አበባው ዘጋቢ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በግንቦት ወር ከሚካሄደው ምርጫ ጋር ተያይዞ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ያዘሉና ገዥውን ፓርቲ የሚተቹ የምርጫ ቅስቀሳዎች በመንግስትና እንደራዲዮ ፋና ባሉ የፓርቲ ልሳናት እየታገዱ ሲሆን ፣ በየመንገዱ የሚሰቀሉና የሚለጠፉ የቅስቀሳ መልዕክቶች

ኢህአዴግ ከፍሎ ባሰማራቸው  ወጣቶች አማካይነት በጠራራ ጸሐይ እየተቀደዱ መሆኑን ፓርቲዎቹ በተናጠል በሚያቀርቡዋቸው ተደጋጋሚ ቅሬታዎች  እያሳወቁ ነው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ተወዳዳሪ ዕጩዎች ሳይቀር ምክንያት እየተፈለገ በመታሰር ላይ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ስጋቶች ላይ የመከረው የአዲስ አበባ ካቢኔ የዋጋ ንረት ፤ የገንዘብ ግሽበት ፤ የስኳር እና ዘይት እጥረቶችን በቀዳሚነት አንስቷል።  በመጭው ምርጫ ለስርአቱ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ነው  ሲል ገምግሟል።

ሙስሊሙ ከፖለቲካው ጋር በፈጠረው ኩርፊያ ፤ ለኢህአዴግ ድምፁን የመንፈግ እና አመፅ የማቀጣጠል እድል እንዳለው ስጋት በሚለው የመጀመሪያ መስመር ላይ ተቀመምጧል፡፡ ምርጫውን ለማሸነፍ የ1ለ 5 አደረጃጀት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሰተያየት ተሰጥቷል።

ካቢኔው በቅርቡ የተከፋፈሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ህዝቡ ለኢህአዴግ ድጋፍ እንዲሰጠው እንደሚያግዘው ገምግመዋል።  ብዙዎችን ያስገረመው  የኮምፒዩተር እጣ አወጣጡን ሶፍት ዌር አዘጋጀው ለተባለው ለመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ወይም ኢንሳ 11 ሚሊዮን ብር መከፈሉ ነው።