9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ “ተረት ተረት” የሞላበት ነበር ሲሉ የቀድሞው የፓርላማ አባል ተናገሩ

መጋቢት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የቀድሞው የፓርላማ አባል፣ የመድረክ ስራ አስፈጻሚና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ም/ል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ገብሩ ገብረማርያም ለኢሳት እንደተናገሩት የኢህአዴግ 9ኛው ጉባኤ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተረት ተረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

“እኛ ትናንት የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙስና መዘፈቃቸውን፣ የሚዲያ ጉዳይ መነጠቁ የዲሞክራሲ ግንባታን የሚገድል መሆኑን” ስንነግራቸው ከቆየን በሁዋላ እነሱ ዛሬ መልሰው ይነግሩናል ያሉት አቶ ገብሩ፣ ተተካካን ይሉና ተመልሰው ሰዎቹ በጓሮ በር ይገባሉ ብለዋል።

” እኛ መተካካት የምንለው ስርአት ሲተካ ነው ” የሚሉት አቶ ገብሩ፣ ኢህአዴግ መተካካት እያለ በህዝብ ላይ እየቀለደ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሆነውን አጥቷል፣ ኑሮው አንገሽግሾታል የሚሉት አቶ ገብሩ፣ ይህች አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን አብረን እንስራ በማለት ያቀረበው ጥሪ የለበጣ እንጅ ከልብ የመነጨ አይደለም ብለዋል አቶ ገብሩ ገብረማርያም

አቶ ገብሩ በ9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የታየው ግንባሩ ወደ እውነተኛውና ወደ ጥንቱ የኮሚኒስት ርእዮተአለሙ እየተመለሰ መሆኑን ከገለጹ በሁዋላ፣  ኢህአዴግ በእሱ ቁመትና  ልክ የምትሆን ጥብቆ አሰፍቶ የኢትዮጵያን ችግር አይፈታም፣ ብለዋል