መንግስት የክልል ነዋሪዎችን በአዲስ አበባ ምርጫ ሊያሳትፍ ነው

መጋቢት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-በመጪው ሚያዚያ ለሚካሄደው የአዲስ አበባና የወረዳ ምርጫዎች የተመዘገበው መራጭ ቁጥር ከተጠበቀው በታች መውረዱ ያሰጋው መንግስት ፣ ከክልል ከተሞች የራሱ ደጋፊ አባላትን በማምጣት በምርጫው እንዲሳተፉ ዛሬ ስልጠና ሲሰጥ ውሎአል።

ከክልል የመጡት ሰዎች በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የስልጠና ጣቢያዎች በመጪው ምርጫ እንዴት ድምጽ እንደሚሰጡ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በነጻነት ትምህርት ቤት  600 ሰልጣኖች ዛሬ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሰልጣኖች ቴክኒካዊ የሆኑ ነገሮችን ሲማሩ መዋላቸውን እና በምርጫው እለት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ግር እንዳይላቸው አስፈላጊውን የሲሙሌሽን ትምህርት ሲማሩ መዋላቸውን በስልጠናው የተሳተፈ አንድ የድርጅት አባል ለኢሳት ገልጿል።

ዛሬ በተሰጠው ስልጠና ከ5 ሺ ያለነሱ ከየክፍለሀገራቱ ተውጣጠው የመጡ የገዢው ፓርቲ አባላት ተሳትፈዋል። በተከታታይ ዙር ስልጠናዎች ሌሎች አዳዲስ አባል መራጮች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሎአል።

ኢህአዴግ ያለማንም ተፎካካሪ ፓርቲ በአዲስ አበባ እንደሚያሸንፍ ቢያውቅም ፣ የመራጩ ቁጥር መቀነስ ፖለቲካዊ ገጽታ ያበላሻል በሚል ስሌት መራጮችን ከክፍለሀገር ማስመጣት ብቻ ሳይሆን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሳይቀር እንዴት እንደሚመርጡ እያሰለጠነ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል።