ታህሳስ 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-87 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መሬት በሊዝ ድርድር እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ውድቅ ያደረገው የ አዲስ አበባ መስተዳድር፤”ሁጃን ግሩፕ” ለተባለው ግዙፍ የቻይና ኩባንያ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል 160 ሄክታር መሬት ሰጠ።
የአዲስ አበባ መስተዳድር የሊዝ ቦርድ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ጥያቄ ውድቅ ያደረገበትን ምክንያት ግልጽ ባያደርግም፣ የከተማው ማኅበራዊና ሊዝ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በደፈናው መሬት በሊዝ ድርድር ለማግኘት የቀረቡ ጥያቄዎች- ተቀባይነት አላገኙም ሲል መግለፁን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ በመሆኑም የመሬት ጥያቄ ያቀረቡ የ አገር ውስጥ አልሚዎች ፕሮፖዛላቸውን ቀርበው እንዲወስዱ ጽሕፈት ቤቱ ጠይቋል፡፡
የመሬት ድርድር ጥያቄያቸው ውድቅ ከሆኑባቸው ኩባንያዎችና ባለሀብቶች መካከል ሸዋ ዳቦና ዱቄት፣ ሉና ኤክስፖርት ቄራ፣ ዑራኤል ሪል ስቴት ዴቬሎፕመንትና አቶ ሳልቫቶሬ ጃኳንቶ ይገኙበታል፡፡
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በሚደነግገው አዲሱ አዋጅ የከተማ መሬት በድርድር እንደማይሰጥ በግልጽ ቢቀመጥም
87ቱ ኩባንያዎች ጥያቄ ያቀረቡት ግን አስተዳደሩ መሬት በድርድር ይሰጥ በነበረበት ወቅት ጊዜ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻገር የከተማው አስተዳደር የመሬትና መሬት ነክ ችግሮችን ለመፍታት ባወጣው መመርያ በድርድር ቦታ የሚሰጥባቸውን ዘርፎች ዘርዝሯል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ፤በመልሶ ማልማት ክልል ውስጥ የንግድና የመኖርያ ቅይጥ ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎችና በአባላቶቻቸው ሙሉ ስምምነት የመሠረቷቸው ማኅበራት የሚያቀርቡት ጥያቄ እንደሚስተናገድ ይገልጻል፡፡
በዚህም መሠረት ባለህብቶቹ የሚፈለግባቸውን መረጃ በማቅረብና በዝግ አካውንት ገንዘብ ገቢ በማድረግ “ጥያቄያችን ይፈቀድልናል” ብለው ሲጠብቁ ቢቆዩም፣ የአስተዳሩ ምላሽ እንደጠበቁት አልሆነም፡፡ “ከባለአደራው አስተዳደር ጀምሮ የምንነግድባቸውን ቤቶች አፍርሰን ግንባታ እናካሂድ ብለን ነው የጠየቅነው፤” ያሉ አንድ መርካቶ አካባቢ የተደራጀ አከሲዮን ማኅበር አባል፣ አሁን ግን በአስተደደሩ ውሳኔ ተስፋችን ተሟጧል” ሲሉ በብስጭት ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት ነክ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላሉ ያላቸውን መመርያዎች ማውጣቱን ተከትሎ፣ አልሚዎች የመሬት ድርድር ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩት ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት ነው፡፡
በሌላ በኩል የ87 የ አገር ውስጥ አልሚዎችን የመሬት ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ይኸው በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዝ ቦርድ፤ አርሶአደሮችን ከይዞታቸው በማፈናቀል ለቻይናው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኩባንያ ሁጃን ግሩፕ- 160 ሔክታር መሬት እንዲሰጥ ወሰኗል፡፡
የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደገለጹት፣ የከተማው መሬት ልማትና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን፤ በቅርቡ ለኩባንያው ቦታውን ያስረክበዋል፡፡
ይሁንና ለቻይናው ኩባንያ 160 ሔክታር መሬት ለምን ያህል ጊዜና በምን ያህል ገንዘብ በሊዝ እንደሚሰጠው ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ለሁጃን ግሩፕ እንዲሰጥ የተወሰነው መሬት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በማስፋፊያ ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ መሬቱ በአርሶ አደሮች እጅ የሚገኝ በመሆኑ፣ በ አሁኑ ጊዜ የከተማው የመሬት ባንክና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ፤አርሶ አደሮቹን ከይዞታቸው በማፈናቀል ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ገብሬ ፣ አርሶ አደሮቹን ከይዞታቸው የማንሳቱ ስራ በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ በመጥቀስ፤ በአንድ ወይም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ቦታው ለልማት ዝግጁ ይደረጋል ብለዋል።
ይሁንና አርሶአደሮቹ ከይዞታቸው ሲፈናቀሉ ስለሚሰጣቸው ካሳም ሆነ ምትክ ቤት፤ ያሉት ነገር የለም።
ቦታውን በቅርቡ ይረከባል ተብሎ የሚጠበቀው የቻይናው ኩባንያ ሁጃን ግሩፕ፤ የጫማ ፋብሪካ፣ ሪል ስቴትና ሆቴል የመሳሰሉ ግንባታዎችን ለማካሄድ እቅድ እንዳለውተገልጿል።
ከሁጃን ግሩፕ ቀደም ብሎ ሌላኛው የቻይና ኩባንያ “ሲጂሲ ኦቨርሲስ” – ለመስተዋት ፋብሪካ ግንባታ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ሰፊ ቦታ መረከቡ ይታወሳል።
በቅኝ ግዛት ዘመን ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻይና ጫማ ስር መውደቋ ይነገራል።
በ አሁኑ ጊዜ በ ኢትዮጵያ ከ 250 የሚበልጡ የቻይና ታላላቅ ኩባንያዎች በተለያዬ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፤ በአብዛኞቹ ኩባንያዎች ውስጥ በ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው መረን የለቀቀ ግፍና በደል- ቅኝ ገዥዎች -በሚያስተዳድሯቸው አገሮች ላይ ይፈጽሙት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የሚከፋ እንጂ የሚያንስ አይደለም ሲሉ በምዕራብ ወለጋ በመንገድ ስራ በተሰማራ የቻይና ድርጅት ውስጥ የሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ፍቅሬ መናገራቸው አይዘነጋም።
የ ኢት ጵያን መሬት በገፍ እየወሰዱ ያሉት እነዚሁ የቻይና አሰሪዎች የአገሪቱን ህግ ያከብሩ ዘንድ በሰራተኛ ማህበራት ለሚቀርብላቸው ተደጋጋሚ አቤቱታና ጥያቄ፦” እኛ የምንመራው በቻይና እንጂ በ ኢትዮጵያ ህግ አይደለም”እስከማለት መድረሳቸውንም ከአቶ ፍቅሬ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።