ለከፍተኛ ስልጠና ወደ እስራኤል የተላኩ ስምንት የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤርትራ ጥገኝነት መጠየቃቸውን “ሀሬትዝ” የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ ዘገበ

18 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የእስራኤል ራዲዮ ያሰራጨውን ዜና በመጥቀስ ጋዜጣው እንደዘገበው፤ ስምንቱ የ ኢትዮጵያ ወታደሮች ለስልጠና ወደ እስራኤል የመጡት ከሶስት ወራት በፊት ሲሆን፤ከሶስት ቀናት በፊት ከማሰልጠኛ ቤዛቸው ጠፍተዋል።

በእስራኤል የኤርትራ አምባሳደር አቶ ተስፋማርያም ተከስተ ፤ወታደሮቹ ባለፈው ሀሙስ ወደ እርሳቸው መኖሪያ ቤት በመምጣት  በኤርትራ የፖለቲካ ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለ እስራኤል ራዲዮ ገልፀዋል።

እንደ ራዲዮው ዘገባ ከስምንቱ ወታደሮች ሦስቱ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፤ወደ አገራቸው ሄደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል ይፈልጋሉ።

አምባሳደሩ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ከሰሙ በሁዋላ ወታደሮቹን በመኖሪያ ቤታቸው በማስቀመጥ በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስታቸው፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት እና ከእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር መነጋገራቸውንም ተናግረዋል።

ከውይይቱ በሁዋላ የ ኤርትራ መንግስት  ለወታደሮቹ ጥገኝነት ለመስጠት ውሳኔ በማሳለፉ፤ባለፈው ረቡዕ በ እስራኤል የ ኤርትራ አምባሳደር የግል አውሮፕላን በመከራዬት ወታደሮቹ ወደ ኤርትራ እንዲበርሩ አድርገዋል-“ሀሬትዝ” የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ እንዳለው።

በሆነው ነገር እጅግ መገረሙን የገለጸው የ እስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከድተው ወደ ኤርትራ ለመግባት ባስተላለፉት ውሳኔ ላይ የ መንግስታቸው እጅ  እንደሌለበት ከወዲሁ አስታውቀዋል።

ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ወደ ጦርነት ያመራሉ የሚል ስጋት እንዳለው ጋዜጣው ጠቁሟል።