(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)
በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ አመት ብቻ 623 ትምህርት ቤቶች በድርቅና በተለያዩ የግጭት መንስኤዎች ምክንያት ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው ተነገረ።
ሲቭ ዘ ችልድረን የተባለው የሕጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያን ትምህርት ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደገለጸው በሃገሪቱ በድርቅና በግጭት ሳቢያ ባለፈው አመት ብቻ 4 መቶ ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።
አለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት እንደገለጸው በምስራቅ አፍሪካ የተወሰኑ ሃገራት ብቻ 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ልጆች በተያዘው አመት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ።
እንደ አለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት ሴቭ ዘ ችልድረን ገለጻ ከሆነ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣በደቡብ ሱዳን፣በሶማሊያና በኬንያ ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟል።
እናም በተያዘው አመት ብቻ 21 ሚሊየን ሰዎች የድርቅ አደጋ መሆናቸውን ሴቭ ዘ ችልድረን ገልጿል።
በተለይ ደግሞ ሕጻናት የዚሁ ድርቅ ሰለባዎች መሆናቸውን ነው ያስታወቀው።
አለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅቱ እንደሚለው በምስራቅ አፍሪካ በተጠቀሱ ሀገራት 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ልጆች በዚህ አመት ብቻ በድርቅ ሳቢያ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።
ድርጅቱ የኢትዮጵያን ትምህርት ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደገለጸው ባለፈው አንድ አመት ብቻ በድርቅና ግጭት ሳቢያ 623 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል።
ይህም በየወሩ 54 ትምህርት ቤቶች እየተገዙ 4 መቶ ሺ ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ነው የተባለው።
በተለይ ደግሞ በኦሮሚያና ሶማሌ ግጭት 1 ሚሊየን ሰዎች ሲፈናቀሉ ከ90 ሺ በላይ ሕጻናት ወዲያውኑ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ የተባበሩት መንግስታት ሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍም መግለጹ ይታወሳል።
ጉዳዩ በእጅጉ ያሳሰበው ሲቭ ዘ ችልድረን ታዲያ በድርቅና በግጭት ሳቢያ የተከሰተው የምግብ እጥረት በእርዳታ እንዲሞላ፣ሕጻናት ለትምህርት ተደራሽ እንዲሆኑና በፖለቲካ ሳቢያ ያለው ቀውስም መፍትሄ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርቧል።