50 የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸው ተነገረ

ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኦጋዴ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፤ከ 50 በላይ የመንግስት ወታደሮችን ገደልኩ ማለቱን ቪኦኤ ዘገበ።

ግንባሩ ጥቃቱን የፈፀመው፤ የ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት  አባላት “ደቦች ሕሪሶ” በተባለ አካባቢ ባለፈው እሁድ ግንቦት 19 ቀን አድርሰውታል ላለው ጥቃት በወሰደው የበቀል እርምጃ ነው።

ኦብነግ ባለፉት ሦስት ወራት ስድስት መኮንኖችን ጨምሮ  በጠቅላላው 168 ወታደሮችን መግደሉን መግለጫው ያመለክታል።

ባለፈው እሁድ የ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ  18 ሰላማዊ ዜጎችን እንደገደለ እና  ከ15 በላይ እንዳቆሰለ የግንባሩ የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባልና  የኢትዮጵያ ጉዳይ ሀላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ተናግረዋል።

የግንባሩ ተዋጊዎች በወሰዱት የበቀልና እስረኞችን የማስፈታት እርምጃ ከገደለቸው ወታደሮች በተጨማሪ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ማቃጠላቸውን፣የተለያዩ መሳሪያዎችንና የሬዲዮ መገናኛዎችን መማረካቸውን እና “ብርቆት”የተባለችን ከተማ ለ 15 ሰዓታት ተቆጣጥረው መቆየታቸውን ሀላፊው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በተጠቀሰው ውጊያ መሳተፋቸውን የጠቀሱና ሻለቃ ሙክታር ሼክ መሀመድ የተባሉ የሶማሌ ክልል ፖሊስ አዛዥ 35 የ ኦብነግ ወታደሮች መገደላቸውን እና 10 መማረካቸውን ለቪኢኤ የሶማሊኛ አገልግሎት ክፍል ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ቀደም ሲል  “ራቅዳ”በተባለች ቦታ አስር ሲቪሎችን ገድሏል፣ዘረፋ አካሂዷል፣የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል”በማለት የሂዩማን ራይትስ ዎች የ አፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ሌፍሊ ሌስኮው ስለሰጡት መግለጫ የተጠየቁት የክልሉ ፖሊስ አዛዥ፦”መግለጫው አንዳችም መሰረት የሌለው የተለመደ የሂዩማን ራይትስ ዎች ፕሮፓጋንዳ ነው”ሲሉ መልስ ሰጥተዋል

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide