ጎንደር ውስጥ የሁለት ሰዎች አስከሬን መሬት ላይ ተጎተተ

ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ታች አርማጭሆ ወረዳ፣ በሳንጃ ከተማ ሸፍተዋል ተብለው በተኩስ ልውውጥ የተገደሉ ሁለት ሰዎች አስከሬን ለሦስት ሰዓታት ያህል መሬት ለመሬት እንዲጎተት ተደረገ።

በድርጊቱ ያዘኑና ጮኸው ያለቀሱ የከተማው ነዋሪዎች በፖሊስ ቆመጥ ተደብድበዋል።

እንደ ፍኖተ ነፃነት ዘገባ፤ ሸፍተዋል ተብለው በተኩስ ልውውጥ  የተገደሉት  የከተማው ነዋሪዎች አቶ ሸንኮና ከፍያለው እና አቶ ዳኛቸው አያሌው ናቸው።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት አቶ ዳኛቸው አካባቢያቸውን ለቀው የተሰወሩት ከአንድ ግለሰብ ጋር ተጣልተው እንጂ፤በመንግስት ላይ ሸፍተው አልነበረም።  ስለ አቶ ሸንኮና ግን በዜናው ላይ የተገለፀ ነገር የለም።

ከዚያም የመንግስት ታጣቂዎች ሁለቱ ግለሰቦች ሸፍተዋል የተባለበትን አካባቢ በመክበብ ተኩስ መክፈታቸውን የጠቀሰው ጋዜጣው፤ እነ አቶ ዳኛቸውም ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ መገደላቸውን አመልክቷል።

ታጣቂዎቹ የሟቾቹን አስከሬን በገመድ አስረው ከቀኑ 8፡00  ሰ ዓት እስከ 11፡00 ሰዓት፤ማለትም ለሦስት ተከታታይ ሰዓት መሬት ለመሬት ከጎተቱ በሁዋላ ከተማው መሀል ላይ በመጣል ህዝቡ እንዲመለከታቸው ማድረጋቸውን  የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤የነበረውን ዘግናኝ ሁኔታ ሲያዩ  እየጮሁ ያለቀሱ የከተማው ነዋሪዎች በፖሊስ ቆመጥ መደብዳባቸውን ተናግረዋል።

በስፍራው በመገኘት ይህን ግፍ በዓይናቸው እንዲመለከቱ የተደረጉት የሸንኮና አባት አቶ ከፍያለውን ጨምሮ እናቱ እና አያቱ አስከሬኑን ወስደው ለመቅበር ቢጠይቁም ተከልክለዋል።

ከዚያም ታጣቂዎቹ የሟቾቹን አስከሬን ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ከከተማው ፖሊስ ጣቢያ ጀርባ በሚገኝ አንድ ትልቅ ዛፍ ላይ ዘቅዝቀው በመስቀል አሳድረውታል።

በማግስቱ እንዲቀበሩ አስተዳደሩ መወሰኑን ተከትሎ የሟቾች ቤተሰቦች አስከሬኑ ተሰጥቷቸው በቤተክርስቲያን መቅበር እንደሚፈልጉ ቢጠይቁም፤ ታጣቂዎቹ በተቀበሉት ትዕዛዝ መሰረት ወጣ ወዳለ ሌላ ቦታ ወስደው እንደቀበሯቸው ተመልክቷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide