4 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሥራ ዝውውር ሊያደርጉ ነው

መስከረም (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሥራ ዝውውር በዚህ ሳምንት እንደሚያደርግ ሪፖርተር ዘገበ።

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ጽሕፈት ቤቱ ዝውውሩን የሚያደርገው በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፋሰስ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር  በሆኑት አቶ ሽፈራው ጃርሶ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ቤኔሉክስ አገሮች አምባሳደር በሆኑት  ዶ/ር ካሱ ኢላላና በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር በሆኑት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ነው።

በሚደረገው ዝውውር መሠረት አቶ ዓባይ ፀሐዬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ሚመደቡ ሲሆን፤ በአቶ ዓባይ ቦታ ደግሞ አቶ ሽፈራው ጃርሶ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ይሆናሉ።

የቤኑሉክስ አገሮች አምባሳደር የነበሩት  ዶ/ር ካሱ ኢላላ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር በመሆን ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑ ሲሆን ዶ/ር ካሱን በመተካት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የአውሮፓ ኅብረትና ቤኔሉክስ አገሮች አምባሳደር ሆነው ወደ ብራሰልስ እንደሚዛወሩ ተዘግቧል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋን በመተካት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የሚሾሙት ደግሞ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ነጋ ፀጋዬ ናቸው።

የባለሥልጣናት የሥራ ዝውውርና ሽግሽግ ሊቀጥል እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ የአራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሚኒስቴር ዴኤታው ምደባ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይፋ ሊደረግ ይችላል ተብሏል፡፡

ቀደም ሲል አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ኩማ ደመቅሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሆነው መመደባቸው ይታወሳል።