መንግስት ከ9 አመታት በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ11 በመቶ በታች እድገት ማስመዝገቡን ገለጸ

መስከረም (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በ2005 በጀት ዓመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 7 በመቶ ማደጉን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር አብርሃም ተከስተ በበርካታ ፈተናዎች ባሉበት ወቅት እንዲህ አይነት እድገት መመዝገቡን አወድሰዋል።

የግብርና ዘርፍ በ2005 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 1 በመቶ የአገልግሎት ዘርፉ  ደግሞ የ4 ነጥብ 9 በመቶ እድገት መመዝገቡ ተገልጿል።

ዶክተር አብርሃም ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የሃገሪቱን አጠቃላይ የምርት መጠን 853 ቢሊዮን ብር ወይንም 47 ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል።

የሃገሪቱ ድህነት  በ2003 ከነበረበት 29 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 26 በመቶ መውረዱንም ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

መንግስት አቶ መለስ ካረፉ በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ11 በመቶ በታች እድገት ማግኘቱን ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የ2005 አመት የእድገት ትንበያ ወደ 5 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማድረጉ ይታወቃል።

ከሁለት አመት በሁዋላ በሚጠናቀቀው የአምስት አመት የእድገት እቅድ መንግስት የ14 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ገልጾ ነበር። ያለፉት 3 አመታት የእድገት አሀዞች መንግስት የእቅዱን ግማሽ ያክል እንኳ ማሳካቱን ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ ናቸው።