ሐምሌ ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ሲሉ፣ 39 የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በፊርማቸው ለህብረቱ ፓርላማ ጥሪ አቅርበዋል። በገዥው ፓርቲ የሚመራው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ያወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ግልጽነት እና ተአማኒነት የጎደለው ነው ሲሉ የፓርላማ አባላቱ ተችተዋል።
የፓርላማ አባላቱ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሞ እና ኦጋዴን ብሔር ተወላጆች ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን፣ ከ2014 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስት ታፍኖ የተወሰደው የሞት ፍርድ የሚጠብቀው እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ጉዳይ እንዲታይ ሲሉ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት አጋርና ቀዳሚው የውጭ እርዳታ ለጋሽ በመሆኑ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ መንግስት ለህብረቱ የማሳወቅ፣ ሙሉ መረጃዎችን የመስጠት ግዴታዎች ይኖርበታል ብለዋል።