በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ

 

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2010) አሁን ከገጠመን አደገኛ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ በአንድነት መታገል አለበት ሲል በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንዲነሳ እና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረትም ጥሪ አቅርቧል።

በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ብሄራዊ መረጋጋትና የሰላም ጥሪ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በማለት ባወጣው ባለሰባት ነጥብ መግለጫ ነባራዊውን የሀገሪቱን ሁኔታ ገምግሟል።

ሀገራችን ወደተሻለ ፍትሀዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የእድገት ጎዳና እንድትጓዝ ብዙ የግዜ፣የገንዘብና የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሏል የሚለው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ህዝባችን የተነሳበትን እውነተኛ ነጻነት፣እኩልነትና ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን የሚያደርገውን ትግል ከምንግዜውም በላይ በጠነከረ ሁኔታ መቀጠል ይኖርበታል በማለት እየተደረገ ያለውን የነጻነት ትግል መጠንከር እንዳለበት አሳስቧል።

መግለጫው ሲቀጥል ያለ ቅድመ ሁኔታ የታሰሩት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ተቀባይነት ያለው የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም፣ የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አሁን ያለውን አለመረጋጋት ከማማባባስ ውጪ የሚፈይደው አንዳች ነገር ባለመኖሩ በአስቸኳይ እንዲነሳ፣ያለፉትን አስከፊ ድርጊቶች ወደኋላ በመተው ከጥላቻ፣ከበቀል፣ ከተንኮልና ከክፋት ነጻ በመሆን ፍትህና ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነትን እንዲወስድ አሳስቧል።

የሀይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በሀላፊነት ቦታ የሚገኙ ዜጎች ሁሉ ከልብ የሆነና ያልተቆጠበ ጥረታቸውን ለሀገር ሰላም እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በተጀመረው የትንሳኤ ጾም ሱባኤ በመጽናት ሁሉም ለሀገሩና ለህዝቡ እግዚአብሔርን እንዲማጸን ጸሎት እንዲያደርግ አሳስቧል።