ጃሬድ ኩሽነር የደህንነት ምርመራን ለማልፍ አለመቻላቸው ተነገረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2010)

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የቅርብ አማካሪና የልጃቸው ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር በኋይት ሃውስ ከፍተኛ ሰነዶችን ለማየት የሚያስችለውን የደህንነት ምርመራን ለማልፍ አለመቻላቸው ተነገረ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከተመረጡ ግዜ አንስቶ ከፍተኛ አማካሪያቸው አድርገው የሾሟቸው ጃሬድ ኩሽነር በጊዜያዊ የደህንነት ፈቃድ አማካሪ ሆነው ቆይተዋል።

እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ ከሆነ ኩሽነር ከዚህ በኋላ በቋሚነት ከፍተኛ ሰነዶችን ለማየት የሚያስችላቸው ፈቃድ ከአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት ማግኘት አይችሉም።

የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ራጅ ሻህ እንዳሉት እስካሁን ድረስ ስራቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል ከዚህ በኋዋላም ቢሆን ኩሽነር በመደበኛ የስራ ቦታቸው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

ቃል አቀባዩ ይህን ይበሉ እንጂ በበርካቶች ዘንድ ኩሽነር ከፍተኛ ሰነዶችን የማግኘት እድል ሳይኖራቸው እንዴት የማማከር ስራቸውን ሊከውኑ ይችላሉ የሚል ጥያቄን አስነስቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን ከመሰንዘር ተቆጥበዋል።

ብዙ ሰራተኞችን በማባረር የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህ አይነቱን ውሳኔ በልጃቸው ባል ላይ ያሳልፋሉ የሚል ግምት እንደሌላቸው ለፕሬዝዳንቱ ቅርበት ያላቸው አካላት መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።