ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአለም እርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) አስታወቀ

ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአለም እርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) አስታወቀ

ኢሳት ( ነሃሴ 27 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ብዙ መሻሻል ባለማሳየቱ፣ አሁንም ድረስ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO) በዚህ በነሃሴ ወር ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎቶችን አስመልክቶ ሰፊ ሪፖርት ባወጣው በዚህ በነሃሴ ወር መግለጫ እንዳመለከተው፣ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በጥር ወር 2008 ከነበረው 10.2 ሚሊዮን ከስድስት ወር በኋላ በነሃሴ 2008 ወር መጨረሻ ወደ 9.9 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል።

ከምግብ ፍላጎት በተጨማሪ የቁም እንስሳት ፍላጎት በሶስት እጥፍ እንደጨመረ የገለጸው ይኸው የፋኦ (FAO) ሪፖርት፣ 2.4 ሚሊዮን ቤተሰብ የቁም ከብቶችቻቸው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ በወጣው ሪፖርት ተመልክቷል።

የቁም ከብቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ ህይወት አዳኝ የሆነ እርዳታ አስፈላጊ መሆኑን ያሰመረው የፋኦ ሪፖርት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአልሚ ምግብ ለቤተሰብ ለማቅረብ የቁም ከብቶችን ደህንነትና ጤና  ላይ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ተመልክቷል።

የአዝመራ ወቅትን የተመለከተ ዘገባ ያካተተው የአለም ምግብ ድርጅት ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት ዘር የሚፈልጉ ገበሬዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመጨረሻ የሆነ አንድ እድል እንደሚቀራቸው ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት 500ሺ የሚበልጥ ቤተሰብ የእርሻ ግብዓቶችን እንደሚፈልግ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ይህ ወር የአዝመራ መዝሪያ ጊዜ የመጨረሻ ወቅት መሆኑን የገለጸው ይኸው ሪፖርት፣ በምግብ ዋስትና ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻልና ዋስትናን ለማረጋገጥ ለገበሬ ቤተሰቦች ዘር በማቅረብ እና የተለያዩ ግብዓቶችን  በማዳረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት እንዲታደጉ ጠይቋል።