ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን አስፍቶ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ኢሳት (ነሃሴ 27 ፥ 2008)

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት አድማሱን አስፍቶ ወደ ተለያዩ አነስተኛ የገጠር ቀበሌዎች ድረስ በተዳረሰበት በአሁኑ ወቅት፣ በሌሎች የክልሉ ዞኖች የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች የህዝባዊ እምቢተኝነት አድማ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በጎንደር እና በጎጃም በሁሉም ከተሞችና የገጠር መንደሮች በአጋዚ ወረራ የታፈነውን ህዝብ ለመታደግ፣ የህዝባዊ እምቢተኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል። ህዝባዊ እምቢተኝነቱ አድማሱ በሰፋ ቁጥር የአገዛዙ ታጣቂ ሃይሎች የመበታተንና ሃይል የማሰባሰብ ሁኔታ ስለማይኖር ህዝባዊ እምቢተኝነቱን እንደሚያፋጥነው ጥሪውን ያቀረቡት አካላት ለኢሳት አስታውቀዋል። በመሆኑም የህዝባዊ ተቃውሞ አድማስ ለማስፋትና የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ ለማድከም ለሁኔታውና ለጊዜ የሚመጥን ተቃውሞ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረብ አስፈላጊ ወቅት በመሆኑ ጥሪው መተላለፉን አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና በኦሮሚያ ክልል መብታቸውን ለመጠየቅ በወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተወስደውን የግድያ ዕርምጃ በመቃወም እንዲደረግ የተጠራው ይህ የህዝባዊ እምቢተኝነት ጥሪ፣ የተለያዩ የህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ ከእነዚህም ውስጥ የስራ ማቆም አድማን ጨምሮ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማን ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።  በአማራ፣ በኦሮሚያና እና በሌሎች ክልሎች በተጠናከረ መልኩ አድማ እንዲካሄድ የታሰበው ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች እስከ ግል ድርጅቶች የህወሃት/ኢህአዴግን አቅም ሊያደክም የሚችል ማንኛውም አድማ እንዲደረግ ተጣይቋል።