በአማራ ክልል  ባለሀብቱ እና ነጋዴው ለአባይ ግድብ ማሰሪያ የሚጠበቅበትን ያህል አስተዋጽኦ አላበረከተም ተባለ፡፡

መጋቢት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፍተኛውን ድርሻ የሸፈኑት የመንግስት ሰራተኞች መሆናቸውም ተገልጿል።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአባይ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ፀሀፊና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣  በአራት አመቱ ውስጥ በክልሉ የተሰበሰበው ገንዘብ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር አካባቢ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ከ384 ሚሊዮን ብር በላይ ከመንግስት ሰራተኛው የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ፣ ከተለያዩ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች በተሻለ መልኩ 57 ሚሊዮን ብር ሲያዋጡ ነጋዴዎችና ባለ ሃብቶች ግን 44 ሚሊዮን ብር ብቻ ማዋጣቸውን ኃላፊው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

በሃገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮች ቢዘጋጁም የተጠበቀውን ያህል ገቢ እንዳልተሰበሰበ የገለጹት ኃላፊው ፤ ከመጋቢት 24/2007 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ቀናት በክልሉ ባሉ ከተሞች በተዘጋጀው የቦንድ ግዢ እንቅስቃሴ አጥጋቢ ውጤት አለመገኘቱ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የግድቡን ስራ በመደገፍ ተገቢውን ማድረግ እንዳለብን ብናውቅም የመንግስት ባለስልጣናት በየደረጃው ስራችንን በአግባቡ እንዳንሰራ  የሚጥሉብን ተገቢነት የሌለው ግብር ስላማረረን በሁሉም እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ይቸግረናል፡፡” ሲሉ ነጋዴዎች ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።

በሌላ በኩል በጎንደር፣በባህርዳርና ደብረታቦር ከተማ የሚኖሩ የመንግስት ሰራተኞች “የግድቡ መሰራት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠቅም ቢሆንም  በአራት አመቱ ውስጥ የተሰበሰበው ገንዘብ ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል እና አብዛኛው ገንዘብ የተሰበሰበው ከመንግስት ሰራተኛው ጉሮሮ ተነጥቆ መሆኑ ዘላቂነቱን አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡”ብለዋል፡፡

ሰራተኞቹ በአሁኑ ጊዜ በመንግስት ያሰራር ጉድለት ምክንያት በተለይ በመንግስት ሰራተኛውና ዝቅተኛ ነዋሪው እየደረሰ ያለው የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝ መሆኑ እየታወቀ፤ ገንዘብ አዋጡ በማለት የሁሉም ፈቃድ ሳይኖር በየጊዜው ከደመዎዛቸው መቆረጡ አግባብነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ባለብን የኑሮ ክብደት ምክንያት ደመዎዛችን እንዲቆረጥ አንፈልግም፡፡” በማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የተናገሩ የመንግስት ሰራተኞች ፣ በየምክንያቱ ከደረጃ ዝቅ እንዲሉና በሰበብ አስባቡ ልዩ ልዩ ቅጣት ሲደርስባቸው መታየቱ፤ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ዝምታን

በመምረጥ በኑሮ ውድነት ለመሰቃየት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በግድቡ ስራ ዙሪያ በመጀመሪያ አካባቢ የነበረው የተነሳሽነትና ቁጭት ስሜት ዛሬ እየጠፋ መሆኑን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች፣  አሁንም “ግድቡ 42 በመቶ ደርሷል የሚለው መግለጫ ትክክል ለመሆኑ ጥርጣሬ አለን” በማለት የገዢው መንግስት ሁልጊዜም በቁጥር በኩል እውነት አለመናገሩ የተለመደ መሆኑን  ይናገራሉ፡፡