የአትዮጵያ መንግስት ሁለቱን የስዊድን ጋዜጠኞች፤ ማርቲን ሽብዬና ዮሀን ፐርሶንን ጨምሮ፤ ለ1900 እስረኞች ምህረት ማድረጉን የተለያዩ አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ።
እስረኞቹ የተለቀቁት የኢትዮጵያን አዲሱን አመት በማስመልከት ባስገቡት የይቅርታ ጥያቄ መሰረት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሞታቸው በፊት፤ በተለይም ለሁለቱ የሰውዊድን ዜጎች ምህርት አድርገው ለአዲስ አመት ሊፈቷቸው እንደነበር ባለስልጣናቱ ገልጸው፤ 1900 እስረኞች በዚህ ሳምንት በሚደረግ የምህረት ስነስርአት እንደሚለቀቁ ታውቋል።
ሁለቱ የስዊድን ዜጎች፤ በሀምሌ 2003 አመተምህረት የኦጋዴን ነጻአውጪ ግንባር እንቅስቃሴን ለመዘገብ፤ ከሶማሊያ ወደኢትዮጵያ ሲገቡ መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንገስት ሽብርተኝነትን በማበረታተት ወንጀል ከሷቸው እያንዳንዳቸው፤ በኢትዮጵያ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት የአስራአንድ አመት ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል።
ሁለቱ ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በወቅቱ የጋዜጠኝነት ስራ ሊሰሩ እንደገቡ ተናግረውየነበረ ሲሆን፤ አለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጠባቂ ድርጅት (ሲፒጄ)፤ እስራቱን አውግዞት ነበር።
ይቅርታ ከተደረገላቸው እስረኞች ዝርዝር ውስጥ፤ በነኤልያስ ክፍሌ መዝገብ 14 አመት እስራት ተፈርዶባቸው የነበረው ወ/ሮ ሂቱት ክፍሌና፤ የአውራምባታይምስ አዘጋጅ ውብሸት ታዬ እንዳሉበት የታወቀ ሲሆን፤ ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ታዋቂ ፖለቲከኘችና የህሊና እስረኞች፤ ርእዮት አለሙ፤ ኦልባና ሌሊሳ፤ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ ከምህረት ዝርዝሩ ውስጥ እንዳሉበት የታወቀ ነገር የለም።