ሳውዲ አረቢያ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ አገደች

(Sep. 10) የሳኡዲ አረቢያ መንግስት፤ ዜጎቹ ወደኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲገቱ ማስጠንቀቂያ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
በአገሪቱ ውስጥ በሙስሊሞችና በፖሊስ መካከከል በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት፤ ግጭቱ እስኪበርድና አገሪቱ ውስጥ ያለው ውጥረት እስኪረግብ ድረስ፤ የሳኡዲ መንግስት፤ ዜጎቹ ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ እንዳስጠነቀቀ እለታዊው የአረብኛ ጋዜጣ፤ አካዝ ጽፏል።
በኢትዮጵያ የሳኡዲአረቢያ አምባሳደር፤ አብዱል በቂ አህመድ አጅላን፤ ከአዲስ አበባ በጻፉት ማስጠንቀቂያ፤ “በረመዳን ወር፤ 7 የሳኡዲ ዜጎች በተለያዩ ስፍራዎች ሲዘዋወሩና የበጎ አድራጎት ስራ ሲሰሩ መታሰራቸውንና በሳኡዲ መንግስት ጥረት ተፈተው ወዳገራቸው መላካቸውን” ጠቅሰዋል።
በኢትዮያጵያ፤ እየጨመረ የመጣውን የሳኡዲ ጎብኚዎች ቁጥር ከግምት በማስገባት፤ ኤምባሲው በአጫጭር የስልክ መልእክቶችና ኤምባሲው በር ላይ በተለጠፈ ማሳሰቢያ፤ ዜጎቹ ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።
እንደ ሳኡዲ ባለስልጣናት መረጃ ከሆነ፤ ባለፈው ሀምሌ ወር ከታሰሩት 7 ሰዎች ውስጥ፤ ሁለቱ የታሰሩት በመርካቶ አካባቢ 20 ላሞችን ሲያከፋፍሉ ተገኝተው እንደሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ሚስት ያለችው ሁለተኛው ሰው የታሰረው በቤቱ በር ላይ ለነዳያን ምጽዋት ሲሰት እንደሆነና፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የታሰሩት በራሪ ወረቀቶችን ሲያድሉ እንደሆነ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ግን 7ቱን የሳኡዲ ዜጎች ያሰርኩት በአገሪቱ ውስጥ የሽብርተኝነትን እንቅስቃሴ ሲደግፉ አግኝቻቸዋለሁ በሚል ጥርጣሬ እንደሆነ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ ከአህባሽ አስተምህሮትና ከመጅሊስ ምርጫ ጋር በተያየዘ፤ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ማሰማታቸውና፤ በዚያም ምክንያት ባለፈው ሀምሌ ወር የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላቱን ጨምሮ፤ ብዙ ሰዎች መታሰራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም የኮሚቴው አባላት በእስር ቤት ሰቆቃና ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ መዘገባችን ይታወቃል።
ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ የሙስሊሞቹ ተቃውሞ የረገበ ቢመስልም፤ በአዲሱ የኢትዮጵያ አመት  በተሌኢም በእስረኞች ላይ በእስርቤት የሚደርስባቸው ሰቆቃ ታክሎበት ተቃውሞው ሊቀጥል እንደሚችል ሙስሊም ተንታኞች ይናገራሉ።