132 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ታሰሩ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 27/2010)132 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ናይሮቢ በፖሊስ መታሰራቸው ተነገረ።

ኢትዮጵያውያኑ በሚኖሩበት መንደር ተከበው የታሰሩት በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብታችኋል በሚል ነው።

በዚሁ አይነት ተመሳሳይ ዘመቻ ሌሎች ተጨማሪ 67 ሰዎች በሌላ አካባቢ ናይሮቢ ውስጥ በጅምላ መታሰራቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ በኬንያ ናይሮቢ በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው ወደ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር የተዘጋጁ እንደነበሩ ዥንዋ በዘገባው አመልክቷል።

ስደተኞቹም በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ የገቡ ናቸው የተባለው በአንድ የናይሮቢ ከተማ ስፍራ ብቻ 132 ኢትዮጵያውያን ሰብሰብ ብለው በደላሎች አማካኝነት ወደ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ዝግጁዎች ነበሩ።

ይህም ሆኖ ግን የኬንያ ፖሊስ በአካባቢው ባካሄደው ዘመቻ ሁሉም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ባለፈው ወርም በተመሳሳይ ሁኔታ 67 ኢትዮጵያውያን በአንድ ስፍራ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ታጭቀው መገኘታቸው ነው የተነገረው።

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ጆሴፍ ጊች አንጊ እንደገለጹት ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በድለላ ስራው የተሰማሩ ሁለት ኬንያውያንም ታስረዋል።

የኢትዮጵያውያኑ እጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን በውል የታወቀ ነገር ባይኖርም በግዳጅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሊደረግ እንደሚችል ግን ፍንጮች አሉ።

የኬንያ መንግስት በሞያሌ የኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሀገር በሚገቡ ኢትዮጵያውያን መማረሩን ገልጿል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በበኩላቸው በሀገራቸው በሚደርስባቸው የሰብአዊ መብት ረገጣና የስራአጥነት ችግር በእጅጉ መማረራቸውን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያው አገዛዝ በኬንያ በስደት ባሉበት በኬንያ ፖሊስ ወረራ ስለታሰሩት ዜጎቹ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

አገዛዙ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ እንደሆነና ይህም ከኬንያ የተሻለ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ለምን ሀገራቸውን ጥለው በብዛት ይሰደዳሉ ለሚለው ጥያቄ ግን የህወሃት ኢሕአዴግ አገዛዝ በቂ ምላሽ ሰጥቶ አያውቅም።

ኢሳት ባልፈው መስከረም ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ባቀረበው ዘገባው በኬንያ ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትዕዛዝ በርካታ ስቃይና በደል እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ረጅም እጅ ባላቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አማካኝነት በኬንያም እየኖሩ ይገረፋሉ፣ከፍተኛ ስቃይም እየደረሰባቸው መሆኑን መረጃው አመልክቷል።

በተለይ በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኬንያ ፖሊሶችን በገንዘብ እየደለለ ስደተኞቹን አሳስሮ ወደ ሀገር ቤት በግዴታ እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑንም ሂዩማን ራይትስ ዎች በመረጃው አመልክቶ ነበር።

የአሁኑ የኢትዮጵያውያኑ አፈሳም የዚህ ውጤት ሳይሆን አይቀርም የሚሉ በርካቶች ናቸው።የኢትዮጵያ መንግስትም ስለ ጉዳዩ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለውም እጁ ስላለበት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።