ነሀሴ ፩ ቀን ፩፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሁኔታው ያሳሰበው የአውሮፓ ህብረት የማልታ መንግስት ያለምንም መዘግየት በእንግልት ላይ የሚገኙትን ሰዎች ወደ ድንበሩ ገብተው ሰብአዊ መብት እንዲያገኙ ጠይቋል፡፡
ማረፊያ ያጣችው መርከብ በውስጧ አራት እርጉዝ ሴቶችን፣ አንድ የተጎዳች ሴትና የ5 ወር ህጻን መያዟን የአውሮፓ ህብረት አስታወቋል፡፡
በላይቤሪያ መንግስት ንብረትነት የተመዘገበችው ጀልባ በግሪካዊ ኩባንያ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረች ሲሆን 120 ኢትዮጵያውያኑንና ኤርትራዊያኑን በሊቢያ ቀይ ባህር ውቅያኖስ ላይ በህገ ወጥ ዝውውር ላይ እንደነበሩ ከአደጋ መታደጓ ተገልጿል፡፡
የጣሊያን የነብስ አድን ሰራተኞች ጀልባው ስደተኞቹን እንደያዘ ወደ ሊቢያ የየብስ ግዛት እንዲያቀና ቢጠየቁትም ጀልባውን በማሽከርከር ላይ የነበረው ካፒቴን ጉዞውን ወደ ማልታ እንዳቀና አውሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ነገር ግን ካፒቴኑ የማልታን የየብስ ግዛት እንዳይገባ የማልታ ባህር ሀይል ከልክሎታል፡
በተፈጠረውም ውዝግብ 120 ስደተኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸው ታውቋል፡፡
ካፒቴኑ በጀልባው ውስጥ ያሉ ስደተኞች አፋጣኝ የህክምና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመናገር ላይ ነው፡፡ የአውሮፓ ህብረት የማልታም ሆነ የጣልያን ባለስልጣናት ውዝግባቸውን ትተው ነብስ የማዳን ስራ ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡
በተለይም በጀልባው ውስጥ በጉዳት ላይ ያለች አንዲት ሴት በአስቸኳይ ሆስፒታል በመግባት ህክምና እንደሚያስፈልጋት ካፒቴኑ በመግለጽ ላይ ሲሆን የማልታና ጣሊያን መንግስት ጉዳዩን እንደሚያጤኑት የአውሮፓ ህብረት በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡
ማልታ ባለፈው ወር ብቻ 1000 ስደተኞች ወደ ግዛቴ ገብተዋል በማለት ጥያቄውን አጣጥላለች፡፡ በማልታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በከፍተኛ ችግር እንዳሉ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡