ጥር ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ዞን በአለታ ጩኮ ወረዳ በጩኮ 02 ቀበሌ በቡድን የተደራጁ ሰዎች የአንድን ነጋዴ ቤት በመዝረፍ ግምቱ 9 መቶ ሺህ ብር የሚያወጣ ንብረት ዘርፈውና ድብደባ ፈጽመው ከተሰወሩ በሁዋላ፣ ድርጊቱን የተቃወሙ የአለታ ጩኮ ጤና አጠባበቅ ጣብያ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ጤና እንዲያዝ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበታል ።
ዝርፍያው የተፈፀመው አቶ ተሾመ የተባሉ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ሲሆን ፓሊስ እና የወረዳው አመራሮች ጥቆማ ቢደርሳቸውም እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል። በቡድን የተደራጁት ሰዎች የሌሎችን ነዋሪዎች ቤቶች ለመዝረፍ ሙከራ ሲያደርጉ፣ ከዳራና ከአለታ ወንዶ ወረዳዎችና ከሲዳማ ዞን የመጡ ፓሊሶች ደርሰው ሌሎች ነዋሪዎችን ከዘርፍያ ታድገዋቸዋል።
በማግስቱ በድርጊቱ ዙሪያ የወረዳው መስተዳድር ህዝባዊ ውይይት ለማድረግ ህዝቡን ቢጠራም ከህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል ። የወረዳው አመራር የነበረና የአለታ ጩኮ ወረዳ የጤና አጠባበቅ ጣብያ ሃላፊ የሆነው አቶ ሰለሞን ጤና ፓሊስ እና የወረዳው አመራር ህዝቡን ቆሞ አዘርፏል በማለት በመተቸቱና ድጋፍ በማግኘቱ ስብሰባው እንዲበተን ተደርጓል። በትችቱ የተበሳጩት የወረዳው አመራሮች የጤና ጣቢያው ሃላፊ ወድያውኑ ባለበት እንዲያዝ የእስር ትእዛዝ አስተላልፈዋል።