475 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የቀላል ባቡር መስመር ምርቃት እያነጋገረ ነው

ጥር ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶስት ተከፍሎ ከሚካሄደው የአዲስአበባ ቀላል ባቡር ግንባታ መካከል ከቃሊቲ እስከ ለገሃር ያለው መስመር ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ በጥድፊያ ባለፈው እሁድ እንዲመረቅ መደረጉና የሙከራ ስራው ለቀጣይ ሶስት ወራት እንደሚቀጥል መታወቁ እያነጋገረ ነው።

የባቡሩ ግንባታ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎችና የመንገደኞች ተርሚናሎች እንዲሁም ከሀያት ወደ ጦር ሃይሎች እና ከፒያሳ የሚነሳው መስመር ግንባታው አልተጠናቀቀም።

የባቡሩን መስመር ለማስመረቅ ጥድፊያ የተሞላበት ሥራዎች ሲካሄዱ የሰነበቱ ሲሆን ባለፈው እሁድ ከአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ጋር በተጉዋዳኝ ለማስመረቅ የታሰበው ሆን ተብሎ ለፕሮፖጋንዳ ጥቅም ታስቦ ነው በማለት የአዲስ አበባው ዘጋቢ ገልጿል።

ባቡሩን በኢትዮጵያዊያን  ባለሙዎች ለመምራትና ለማንቀሳቀስ በውጪ ሀገር መሰልጠናቸው ቢነገርም፣  ለቀጣይ አምስት ዓመታት የባቡሩን ማኔጅመንት ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት የቻይና ኩባንያዎች የሆኑት ሲ አር  ኢ ሲ እና ሺን ዜን  ይሆናሉ ተብሎአል።  ቻይናውያን ኩባንያዎች ለማኔጅመንቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይከፈላቸዋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ባይኖር ኖሮ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር የመሳሰሉ ግንባታዎች እንደማይካሄዱ በማስመሰል የሚሰራጨው ቅስቀሳ በመጪው ምርጫ የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ታስቦ መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል፡፡

በቀጣይ ሳምንታትም የአዲስአበባ ኮንዶሚኒየም፣ 40 በ60 እና 10 በ90 የሚባሉ ቤቶች በዕጣ ለሕዝብ በማስተላለፍ ተከታታይ ፐሮፖጋንዳ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቅሰዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታ  475 ሚሊየን አሜሪካን ዶላር የተመደበ ሲሆን፣  85 በመቶ የሆነው ገንዘብ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘ ነው።