ፕሬዚዳንት ኦባማ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ

መስከረም ፲፮(አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የተገናኙነት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በሰላም ማስጠበቅና ሽብርተኝነትን በመዋጋት በኩል እያደረገች ያለውን ሚና አወድሰዋል።

አገሪቱ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም በማስጠበቅ በኩለ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ  የሰላም አስከባሪ በመላክ ቁጥር በአለም ግንባር ቀደም ከሆኑ መንግስታት ተርታ እንደምትመደብም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ቦይንግ

አውሮፕላን ለመግዛት ውል መፈጸሙ በአሜሪካ ውስጥ ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠሩን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አገራቸው ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ያላት መሆኑን አክለዋል።

በዚህ አመት ስለሚደረገው ምርጫ የተወሰነ ነገር አውቃለሁ ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ መንግስት ምርጫው ለአፍሪካ ምሳሌ እንዲሆን መስራት እንዳለበት፣ ለሲቪክ ሶሳይቲው ተሳትፎ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ስለምትሰጠውን ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊቷን ለሰላም ማስከበር አግልግሎት በመላኩዋ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያገኘችና የሰራዊቱም ህይወት እየተለወጠ መሆኑን የአማራ ክልል ብሄራዊ ተጠባባቂ ጽ/ቤት ሃላፊ ኮ/ል አበበ በየነ ገልጸዋል።