ፑቲን ጦራቸው በዩክሬን ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን ተናገሩ

የካቲት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሩስያው ፐሬዚዳንት ቭላድሜር ፒቲን ዩክሬን የሚገኘው ጦራቸው በአገሪቱ የሚገኙ ሩስያውያንን ከመጠበቅ ውጭ ምንም እርምጃ አለመውሰዳቸውን ለጋዜጠኖች ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙት ሩሲያውያን እርዳታቸውን ከጠየቁ፣ አገራቸው በዩክሬን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ግልጽ አድርገዋል።

የሩሲያ ጦር የዩክሬንን ግዛት መውረሩን ተከትሎ በምእራባዊያን እና በሩሲያ መካከል ሰሞኑን የተፈጠረው ውዝግብ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ፑቲን በሩሲያ ላይ የሚጣለው ማእቀብ ሁሉንም ወገኖች ይጎዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ ኬቭ ለሚገኘው አዲሱ የዩክሬን መንግስት እውቅና ባትሰጥም፣ ከስልጣን የተወገዱት ቪክቶር ያንኮቪች መጻኢ የፖለቲካ ህይወት ይኖራቸዋል ብላ ሩሲያ እንደማታምን ፕሬዚዳንት ፑቲን ገልጸዋል።

ሩሲያ መላውን ዩክሬን ለመውረር እቅድ ካላት የአውሮፓ አህጉር የጸጥታ ሁኔታ አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ብዙ ተንታኞች ይናገራሉ። አንዳንድ የዩክሬን መሪዎች የሩሲያ ታክቲክ ክሬሚያን ማስገንጠል መሆኑን በመግለጽ የአለም ህዝብ እንዲደርስላቸውም ተማጽነዋል። ፑቲን በበኩላቸው ክሬሚያን የመገንጠልም ሆነ ያለመገንጠል ፈቃድ የህዝብ እንጅ የሩሲያ አይደለም ብለዋል።

የፕሬዚዳንት ፑቲን መግለጫ በአካባቢው የተፈጠረውን ውጥረት እንደማያረግበው ተንታኞች ይገልጻሉ። የፕሬዚዳንት ኦባማ የመሪነት ችሎታ ይፈተንበታል በሚባለው በዚህ ቀውስ፣ አሜሪካ በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ እንዲጣል እየሰራች መሆኑን ኦባማ ተናግረዋል። ከ25 በመቶ በላይ የነደጅ ፍጆታውን ከሩሲያ የሚሸምተው የአውሮፓ አህጉር በማእቀቡ ክፉኛ የሚጎዳ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ የአውሮፓ መሪዎች ጠንካራ ማእቀብ እንዳይጣል ይፈልጋሉ።

እንግሊዝ ማእቀብ መጣሉን ሃሳብ እንደማትደግፈው ፍንጭ ሰጥታለች። ጀርመን በበኩሉዋ ከሩሲያን ጋር የመፍትሄ ሃሳብ ለማፈላለግ እየሰራች መሆኑን ተናግራለች።