ሼክ ሁሴን ሙሀመድ አላሙዲ በአለም 61ኛው ባለሃብት ተባሉ

የካቲት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከኢትዮጵያና ሳውድ አረቢያ ወላጆች የተወለዱት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት ሼክ ሙሀመድ አላሙዲን፣ በያዝነው አመት አጠቃላይ ሀብታቸው 15 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ፎርቢስ መጽሄት ይፋ አድርጓል።

ሼክ አላሙዲን በነዳጅ፣ በማእድንና በግንባታ ስራዎች ከፍተኛ ሀብት ማካበታቸው ተመልክቷል። ባለሀብቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢነቨስትመንት ያላቸው ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጠሩ በሚያስቀምጡዋቸው ቦታዎች መንግስት እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑ ይነገራል። ሼህ አላሙዲን ከ15 አመታት በላይ አጥረው ያስቀመጡዋቸውን ቦታዎችን ለምን እንደማያለሙዋቸው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው፡፡ መንግስትም በሌሎች ባለሀብቶች ላይ የሚወስደውን እርምጃ በሼክ አላሙዲን ላይ ለመውሰድ እንደሚቸገር ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

ሼክ አላሙዲን የኢትዮጵያን የወርቅ ማምረቻ ጉድጓዶችን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ተቋማትን መግዛታቸው ይታወቃል። በዘንድሮው የደረጃ ሰንጠረዥ ናይጄሪያዊው ቱጃር አሊኮ ዳንጎቴ በ25 ቢሊዮን ዶላር አንደኛ ሲሆኑ፣ የማይክሮ ሶፍት ባለቤት የሆኑት ቢል ጌትስ ደግሞ በ67 ቢሊዮን ዶላር የአንደኝነቱን ደረጃ ይዘዋል።