ግንቦት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምርጫ ቦርድ ትእዛዝ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ፣ ግንቦት 25/2007 ዓም
ፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቁ ቢወስንም ፣ ፖሊስን ግን መልሶ አስሯቸዋል።
አቶ ማሙሸት ሚያዚያ 14፣ 2007 በአይ ኤስ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን በማስመልከት ድርጊቱን ለማውገዝና ኢትዮጵያውያኑንም ለመዘከር በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የታየውን ረብሻ አደራጅተዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም፣
አቶ ማሙሸት ግን በተባለው እለት እርሳቸው በሌላ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ እንደነበሩ የሚያሳይ ተጨባጭ ማስራጃ በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቷቸዋል።
ይሁን እንጅ የመፈቻ ዋራንት ከተጻፈ በሁዋላ፣ አቶ ማሙሸት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ተወስደው መታሰራቸውን የፓርቲው ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ አቶ ለገሰ ወልደሃና ለኢሳት ተናግረዋል ። በዛሬው እለት ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ጉዳያቸው
በዝግ ችሎት መታየቱን የገለጹት አቶ ለገሰ፣ በአዲሱ ክስ “ሚያዚያ 12 እና 13 የተነሳውን ተቃውሞ አደራጅተሃል እንዲሁም ወጣቶቹን ወደ ኤርትራ እልካለሁ እያልክ ታደራጃለህ” የሚል መካተቱንም አክለዋል።
በተመሳሳይ ዜናም የቀድሞ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ፀሀፊ የነበረው አቶ ፋንቱ ዳኜ ISIS ለማውገዝ በተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ረብሻ አነሳስተሃል ተብሎ አንድ አመት ከሁለት ወር ተፈርዶበታል።
ከዚሁ ከእስር ዜና ሳንወጣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ ወንድምአገኝ አስፋው ፖስተር ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አካባቢዎች ለጥፈሃል በሚል መታሰሩን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ሌላዋ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው ወ/ሮ ንግስት ወንዲፍራው ክስ ተመስርቶባታል። በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት የቀረበችው ወ/ሮ ንግስት፣ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በነበረው ሰልፍ ላይ
‹‹ወያኔ ሌባ፣ መንግስት አሸባሪ፣ ታርዷል ወገኔ፣ ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ፣ ወያኔ አሳረደን፣ ናና መንግስቱ ናና፣ ወያኔ አሸባሪ…በማለት እጅን አጣምሮ ወደላይ በማድረግ ታስረናል›› በማለት ሰላማዊ ሰልፉ በመምራትና በማወክ መከሰሷን
የክስ ቻርጁ ያመለክታል።
በሚያዝያ 13/2007 ዓ.ም ቂርቆስ አካባቢ ‹‹ስብሰባን ወይም ጉባኤን›› በማወክ ተከሳለች።