ፍርድ ቤት አቶ ማሙሸት አማረ ዋስትና ተከልክለው ወደ ቅሊንጦ እንዲላኩ ወሰነ

ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ችሎቱን የተከታተሉት በአቶ ማሙሸት የሚመራው መኢአድ ምክትል ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለኢሳት እንደገለጹት አቶ ማሙሸት፣ ሰኔ 10፣ 2007 ዓም በ5 ሺ ብር ዋስ እንዲወጣ ፍርድ ቤት የወሰነ ቢሆንም፣ ፖሊስ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ዛሬ ፍርድ ቤት አቅርቦታል።
ፖሊስ፣ አቶ ማሙሸት ቢፈታ በምስክሮቼ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሊያደርስባቸው ይችላል የሚል ይጋባኝ ያቀረበ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም የፖሊስን ጥያቄ በመቀበል አቶ ማሙሸት ቂልንጦ እስር ቤት ወርዶ ከ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በሁዋላ ሰኔ 29 ይቅረብ ሲል አዟል።
አቶ ማሙሸት በአዲስ አበባ አይ ኤስ ኤስን ለማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ የታየውን ተቃውሞ አስተባብሯል ፣ ወጣቶችን በማስተባበር ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ አድርጓል እንዲሁም ከውጭ አገራትም ምንጩ ካልታወቀ ሃይል ገንዘብ ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ሌላው የመኢአድ የውጭ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብርሃም ጌጡም እንዲሁ ፍርድ ቤት ቀርቧል። አቶ አብርሃም ሚያዝያ 13 /2007 ዓም ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ፣ ሚያዝያ 14/2007 ዓም በአይ ኤ ኤስ የታረዱትን ወገኖች ለማውገዝ መንግስት የጠራውን ሰልፍ ወጣቶችንን አደራጅተህ እንዲበጠበጥ አድርገሃል፣ የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን፣ ተከሳሹ ግን ክሱን አጣጥሎታል። አቶ አብርሃም ” በሙያየ አካውንታንት ነኝ፣ በርከታ ደንበኞች አሉኝ፣ ወቅቱ የበጀት መዝጊያ ነው፣ እንዲሁም ተመራቂ ተማሪ ነኝ ብዙ ሀላፊነት አለብኝ የዋስ መብቴ ይከበርልኝ” ሲል ቢያመለክትም፣ ፍርድ ቤት ግን የ4 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሹ፣ ለ ሰኔ 19 /2007 ዓም እንዲቀርብ ማዘዙን አቶ ለገሰ ተናግሯል።
በወሎ የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነው ሞገስ አሰፋም እንዲሁ ሰኔ 13 ቀን 2007 ኣም ተይዞ መታሰሩ ታውቓል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በቅርቡ የተገደለውን የወጣት ሳሙኤል አወቀን ሀዘን ለመድረስ የሄዱ የትግል አጋሮቹ ታገቱ
ስኔ 8፣ 2007 ዓም በደብረማርቆስ ከተማ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደሉ የተገለጸውን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ሳሙኤል አወቀን ቤተሰቦች ሀዘን ለመድረስ የተንቀሳቀሱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት በፖሊስ ታግተው ከቆዩ በሁዋላ ምርምራ ተካሄዶባቸው መለቀቃቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ገልጿል።
በእለቱ በቦታው የነበረው ዋና ዘጋጁ አቶ ጌታቸው ሽፈራው ለኢሳት እንደገለጸው፣ አመራሮቹ ከቀኑ ስምንት ሰአት እስከምሽቱ 2፡30 ድረስ ታግተው ነበር ብሎአል። በእገታው ስልኮቻቸውና ሌሎች እቃዎቻቸው መወሰደቻውንም ገልጿል።
ከአዲስ አበባ የሄዱ የደህንነት አባላት እንደነበሩ የሚገልጸው ጌታቸው፣ ጎሃጽዮን ሲደርሱ ምርምራ እንደተደረገባቸው ተናግሯል። ምርመራው ሳሙኤል ማን ገደለው የሚለውን ይጨምር እንደነበር አክሏል።
ታግቶ የነበረው መኪና ዛሬ ጠዋት ቢለቀቅም፣ ካሜራ ጨምሮ የተያዙት ሌሎች ቁሳቁሶች ግን አለመለቀቃቸውንም ጌታቸው አክሎ ገልጿል።