ፌደራሊዝም የተሻለ የፖለቲካ አስተዳደር ስርአት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011) ክልላዊ አስተዳደርን ከብሔር ማንነት ጋር ሳናምታታ ማስተናገድ ከቻልን እንደ ኢትዮጵያ ላለች ሃገር ፌደራሊዝም የተሻለ የፖለቲካ አስተዳደር ስርአት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።

በሃዋሳ ዛሬ በተከፈተው የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሁሉም ክልላዊ አስተዳደሮች ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተዳድሩ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የተረከብናትን ኢትዮጵያን አለመውደድ መብታችን ነው አስውበን ማስረከብ ግን ግዴታችን ነው ሲሉም ዶክተር አብይ አህመድ በሃዋሳ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጭምር የተገኙበት የሃዋሳ ጉባኤ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን አመራር በመምረጥ እንደሚጠናቀቅም ተመልክቷል።

አዲስ ታሪክ ለመጻፍና ለመስራት የሚያስችል የዘመን አካፋይ አንጓ ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሃገራችን የለውጥ መህዋር ውስጥ እንደምትገኝ አመልክተዋል።

ይህም ለውጥ ከውስጥ በመነሳቱ ያስገኘውን ፋይዳም ሲያስቀምጡ እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ሕይወት ከውጭ ሲሰበር ደግሞ ሞት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የቀዳሚ ስልጣኔ ባለቤት በነበረችው ሃገራችን በላቀ ተግባራቸው ያገነኗት መሪዎች የመኖራቸውን ያህል ለውድቀት የዳረጓትና ለጠላት የሰጧት መሪዎችም ገጥመዋታል ብለዋል።

በሕዝቧ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ያደረጉ መሪዎች የመኖራቸውን ያህል በሕዝቡ መካከል መተማመን እንዳይኖር ያደረጉ መኖራቸውንም አስታውሰዋል።

ዛሬ ላይ ሆነን ትላንትን ማስተካከል አንችልም፣የኛ ተግባር የነገውን ማሳመር ነው ያሉት ዶክተር አብይ አሕመድ የተረከብናትን ኢትዮጵያን አለመውደድ መብት ቢሆንም አስውበን ለልጆቻችን ማስረከብ ግን ግዴታችን ነው ብለዋል።

ዘርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገን ሌሎችን አናጥቃ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አንዱ አካባቢ ለሌላ ጤና ሊሆን አይችልም ብለዋል።

እርስ በርሳችን እንደጋገፍ እንጂ አንፎካከር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኢትዮጵያ ሁኔታ ፌደራሊዝም ተመራጭ ስርአት ነው በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ክልላዊ አስተዳደር ግን ከብሔር ማንነት ጋር መምታታት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።