ፋሽስት ግራዚያኒን ለመቃወም ለሁለተኛ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተጠራ

የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-በቅርቡ የኢጣልያ መንግስት ለፋሽስቱ የጦር ወንጀለኛ ለማርሻል ግራዚያኒ ያስገነባው ሙዚየምና የመናፈሻ ስፍራን ለመቃወም በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተጠራ።

እንደ ሰንደቅ ዘገባ የተቃውሞ ሰልፉን የጠሩት ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣ ባለ ራዕይ የወጣቶች ማኅበር እና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው።

ቀደም ሲል ሦስት በጎፈቃድ አባላት ያሉበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ተቆርቋሪ አባላት፤ የካቲት 30 ቀን 2005 ዓ.ም የተቃውሞ ሰልፉን ለመጥራት የአዲስ አበባ አስተዳደርን በደብዳቤ ቢያሳውቁም ምላሽ አላገኙም ነበር።

በመሆኑም  የተቃውሞ ሰልፉን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ለመምራት የሲቪክ ማኅበር የሆነው ባለ ራዕይ የወጣቶች ማኅበርና ሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ሲል ከተቋቋመው “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ” ጋር በመሆን እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍልን ጠይቀዋል።

መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ የሚደረግ ነው።

በሰልፉም ላይ ፋሽስት ኢጣሊያን በወቅቱ በሀገራችን ላይ ላደረሰው ግፍ የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን የጦር ወንጀል እንዲመዘግብ፣ በፋሽስት ኢጣልያ አማካኝነት ከሀገራችን የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ፣ በፋሽስቶች አማካኝነት በሀገራችን ላይ ለተፈፀመው እልቂትና ውድመት የኢጣሊያ መንግስት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍልና ለጦር ወንጀለኛው ለማርሻል ግራዚያኒ የጣሊያን መንግስት በቅርቡ የገነባው መካነ-መቃብርና  መናፈሻ ሥፍራ እንዲፈርስ በይፋ ጥያቄ ይቀርብበታል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ኃላፊ አቶ ማርቆስ፤የተቃውሞ ሰልፍ ጥያቄው በደብዳቤ ለክፍሉ መድረሱን ገልፀው፤ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጥ አካል ውሳኔ ይሰጥበታል ብለዋል።

በጣሊያን ወረራ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ከተፈፀሙ አስከፊ ድርጊቶች መካከል 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከየካቲት 12 እስከ 15 ቀን 1929 ዓ.ም ባሉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የተገደሉ ሲሆን፤ በርካታ አብያተ ክርስቲያኖችና ቤቶችም ወድመዋል።

እንዲሁም  በአውሮፕላን በተረጨ የመርዝ ጋዝ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ እንስሶች አልቀዋል ከማለቃቸውና አስከፊ የአካባቢ ብክለት ከመድረሱም በላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እስር፣ ልዩ ልዩ እንግልትና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል።